የአድዋ ድል ቀን ተከበረ

                             መቶ ሃያ ሶስተኛው የአድዋ ድል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ

የ2011 ዓ.ም. የአድዋ ድል በሁለት አበይት ክዋኔዎች ታስቦ ውሏል፡፡ አንደኛው  መነሻውን ጊዮርጊስ አደባባይ በማድረግ  እለቱን ለመዘከር የተደረገ የእግር ጉዞ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዋናው ግቢ መሰብሰቢያ አዳራሽ  ይህን ታሪካዊ ቀን በማውሳት የተደረገው ትምህርታዊ ውይይት ነው፡፡

በበዓሉ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳኝነት አያሌው ታዳሚውን  የሚያነቃቃ ንግግር  አድርገዋል፡፡ አቶ ዳኝነት በንግግራቸው አልደፈር ባይ የአድዋ ጀግኖች አባቶቻችን ፍፁም በሆነ መንፈሳዊ ፅናት በዱር በገደል፣ በእግር በፈረሰ ተዋግተው ያቆዮዋትን ነፃ አገር፤ ወጣቱ ትውልድ ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ፡፡

በዩኒቨርሲቲው ባህል ማዕከል እና የታሪክ ቅርስ አስተዳደር የጋራ ትብብር በተደረገው ውይይት  ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በዘመኑ ተንሰራፍቶ የነበረውን አፍሪካን እና ሌሎች የአለም ክፍሎችን የመቀራመጥ የአውሮፓዊያን የእብሪት አጀንዳ በሀይል መስበር እንደሚቻል ያሳዩበት አንፀባራቂ ድል መሆኑ በኩራት ተወስቷል፡፡

በእለቱ የዩኒቨርስቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንደተናገሩት አድዋ ለመላው ኢትዮጵያውያን በነፃነት ለመቆማችን ምስክር ከመሆንም አልፎ ለጥቁር ህዝቦች ታላቅ ድልና  ዘመን ሳይሽረው በሁሉም ልብ ተፅፎ ከትወልድ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ የኩራት ምንጭ ነው ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ የአድዋ አንፀባራቂ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በቅኝ ግዛት ለነበሩት ሁሉ የነፃነት ተምሳሌት እንደሆነ ፕ/ር ሹመት ሲሻኝ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ከአድዋ የምንወስዳቸው ትምህርቶች እና የሴቶች ሚና በአድዋ የጦር ሜዳ ውሎ በሚሉ ርዕሶች ፅሁፎች ቀርበው በታዳሚዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

በመጨረሻም የዛሬው ትውልድ ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳይሆን ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ተጠቅሞ ያለፈውን፣ ዛሬን ብሎም ነገን  ባገናዘበ መልኩ ለአገሩ የተሻለ እድገት ለማምጣት እንዲተጋ የቃልኪዳን ምልክት የሆነውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አርማ ከአባት አርበኞች ተረክቧል፡፡