የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም ስርዓተ-ትምህርት ክለሳ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም የስርዓተ ትምህርት ክለሳ አካሄደ
---------------------------------------------------------------------------------------
በሙሉጌታ ዘለቀ

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም የእሳት ፤ ደህንነት እና የአደጋ ጊዜ የስራ አመራር ስልጠና እና ምላሽ ማዕከል ለማቋቋምና ሦስት አዲስ አጫጭር የስልጠና ስርዓተ-ትምህርቶችን ለመከለስ የውይይት መድረክ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ግቢ ተካሂዷል፡፡

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር አዳነ ተስፋዬ  እንደተቋም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ራዕይና ተልኮ ግምት ውስጥ በማስገባት የህብረተሰቡን ችግር በመረዳት በከተማችን ብሎም በክልላችን እና በሀገር ደረጃ በእሳት አደጋ ምክንያት በርካታ የሰው ህይወት እና የቁሳቁስ ውድመት እንደሚደርስ ጠቁመው ችግሩን መቀነስ ይቻል ዘንድ አጫጭር ስልጠናዎችን ለመስጠት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የዳሰሳ ጥናት ተካሂዷል ብለዋል፡፡ ጥናቱን በመመርኮዝመ የእሳት ፤ ደህንነት እና የአደጋ ጊዜ የስራ አመራር ስልጠና እና ምላሽ ማዕከል ለማቋቋም በዕለቱ የስርዓተ ትምህርት ክለሳ በባለሙያዎች እያደረገ መሆኑን ዶ/ር አዳነ ተስፋዬ  ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር አዳነ  አክለውም አቅምን በማጎልበት ከዲፓርትመንት ወደ ተቋም ማደግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አቶ ይልበስ አዲሱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም መምህር እና ምክትል ዳሬክተር እንዳሉት የእሳት አደጋንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ሀላፊነትን ወስዶ የሚሰራ ተቋም እንደሌለ ገልፀው፤ በሀገር ደረጃ በመዲናይቱ አዲስ አበባ ብቻ እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ይህም ተቋም  እሳት አደጋን ብቻ መሰረት አድርጎ የሚሰራ በመስኑና ሌሎች ተያያዥ የደህንነትና የድንገተኛ አደጋን ባለመስራቱ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጥናት ተቋም የእሳት ፤ ደህንነት እና የአደጋ ጊዜ የስራ አመራር ስልጠና እና ምላሽ ማዕከል ለማቋቋም የስርዓተ ትምህርት ክለሳ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በእለቱም አቶ ስንታየሁ አዳባ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ Occupational safety & health ስርዓተ-ትምህርትን፣ ወ/ሮ በለጡ ተፈራ በአዲስ አበባ ከተማ  የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተቋም ነባር ባለሙያ Emergency management system ስርዓተ-ትምህርትን፣  አቶ አሸናፊ ቶላ በአዲስ አበባ ከተማ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር እና ዶ/ር ታደሰ መለሰ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነባህሪ ኮሌጅ ዲን  Fire risk management ስርዓተ-ትምህርት ረቂቅን  ገምግመዋል፡፡ እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት በመጡ  እንግዶችና ታዳሚዎች አስተያየቶች ቀርበው ከአቅራቢዎችና በፕሮግራሙ ተሳታፊ በሆኑ መምህራን ግብረ-መልስ እና ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ብርሀኑ ገድፍ በውይይቱ ላይ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር በምስረታ ሂደት ላይ ያለው ተቋም ከሀገራችንም አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን በሙያው የሰለጡ ባለሙያዎች የበለጠ እውቀትንና ልምድን ማግኘትና ይህንን ውጥን ተግባር የበለጠ መሬት እንዲነካ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው በኩል ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ ለተቋሙ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ተጠንተው እንዲቀርቡ አሳስበው ለተፈፃሚነቱ አፈላጊውን እንደሚያደርጉ በአፅኖት ተናግረዋል፡፡