የችግኝ ተከላ ተካሄደ

                                     በቤዛዊት ተራራ ላይ የችግኝ ተከላ ተካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንቱን ጨምሮ በተለያየ ደረጃ ላይ ያሉ አመራሮች ፣ መምህራንና በሁሉም ግቢ ያሉ የ2011 ዓ.ም. ተመራቂ ተማሪዎች ባሕር ዳር በሚገኘው የቤዛዊት ተራራ ላይ የችግኝ ተከላ ዛሬ ሐምሌ 6፣ 2011 ዓ.ም. አካሄዱ ፡፡

የችግኝ ተከላው የተከናወነበት የቤዛዊት ተራራ በባሕር ዳር በስተ ሰሜን ምስራቅ የሚገኝ ሲሆን በከተማዋ የአገሪቷ መሪዎች ማረፊያ ስፍራ ሆኖ ያገለግል የነበረ  ሲሆን ከዛሬ አርባ አመት በፊት ደግሞ በደን የተሸፈነ ቦታ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ስዓት አካባቢው የተራቆተ ከመሆኑ ባሻገር ሌሎች የዛፍ ዝርያዎችን አንቆ ይዞ ብቻውን በሚስፋፋ የወፍ ቆሉ በሚባል  አረም በመዋጡ የችግኝ ተከላው አረሙንም ለማስወገድ እንደሚጠቅም ተጠቁሟል፡፡ የዚህ አመት ተመራቂ ተማሪዎች የሆኑት በምረቃ ወቅት ከሚያዘወትሩት የማስታወሻ ፎቶ ከመነሳት ባሻገር በእለቱ በችግኝ ተከላው መሳተፋቸው ከከተማዋ እና ከዩኒቨርሲቲው ጋር የሚኖራቸውን ትዝታ ህይወት እንዲኖረው እንደሚያደርግ ይታመናል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ  እንዳሉት ችግኝ መትከል በተከታታይ ሊከናወን የሚገባ እንደሆነ ገልፀው ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በዘለቄታ መንከባከቡ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ፕሬዝደንቱ አክለውም እግኞችን መንከባከብ የእያንዳንዱ የማህበረሰብ ክፍል ድርሻ እንጅ ለተወሰኑ ግለሰቦች ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁላችንም የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም ተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ የሁሉም እድገታችን መሰረት ነው ብለዋል ፡፡

የችግኝ ተከላው ፕሮግራም አስተባባሪና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ አብይ መንክር በበኩላቸው  አካባቢው ድንጋያማ በመሆኑ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ የግራቢያ ችግኞችን ከሶሳይቲ ኢኮ-ቱሪዝም ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ችግኞች እንደተተከሉ ገልፀዋል፡፡ በዚህም ተግባር የተራቆቱ ተራራማ ቦታዎችን ከዚህ በፊት ወደ ነበሩበት ለመመለስ በቀጣይም በሚመለከታቸው የግብርና ባለሙያዎች ክትትል ተጨማሪ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል ፡፡አክለውም የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ በማሰብም በቦታው የሚገኘውን ሳር እያጨዱ እንዲወስዱ እና ከፓርኩ ዘለቄታዊ ጥቅም እንዲያገኙ ደግሞ ንብ አንበው እንዲጠቀሙ ይደረጋል ብለዋል ፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጋዥነት የተደራጁት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ አባል የሆኑት አቶ መዝገቡ ተገኘ እንደገለፁት ማህበረሰቡ በልቶ የጨረሰውን ተፈጥሮ ሀብት ወደ ነበረበት ለመመለስ እርሳቸውን ጨምሮ ሶስት ሺህ ከሚሆኑት አባላት ጋር በመሆን ችግኞችን በመንከባከብ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በችግኝ ተከላው በአጠቃላይ እስከ 1500 የሚጠጉ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ከ15000/አስራ አምስት ሺሀ/ በላይ ችግኞችንም ከጠዋቱ 3 ስዓት እስከ 5፡30 ባለው ጊዜ ውስጥ መትከል ተችሏል፡፡