የቤነፊት ሪያላይዝ የመስክ ምልከታ

በአርሶ አደሩ ማሳ ሰርቶ ማሳያ የመስክ ምልከታ ተደረገ
*********************************************
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም በወገራ ወረዳ ሰንበትጌ ቀበሌ የአርሶ አደሮችን የመስክ ቀን የተለያዩ የመንግስት ተቋማት በተገኙበት የመስክ ምልከታ ተደረገ ፡፡
 
በዕለቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የወገራ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ ሰማኸኝ መከተ የምርምር ውጤት ብዙውን ጊዜ ወደ ተጠቃሚው ህብረተሰብ አውርዶ ተግባራዊ በመድረግ በኩል ሠፊ ችግር ያለበትና ሸልፍ ላይ ተቆልፎ የሚቀመጥ ሆኖ እንደቆየ ተናግረዋል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) የምርምር ውጤት በወረዳችን ላይ ይዞ በመግባት ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም እስካሁን የዝናብ አጠር አካባቢ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በቅድመ ማስፋት ተግባር ለ64 አርሶ አደሮች በስርዓተ ምግብ አመጋገብና በስንዴ ምርት አመራረት የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ሲሆን ዛሬም የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በእለቱም የዚህ ትልቅ ተግባር ማሳያ የሆነውን በሰንበትጌ ቀበሌ በ10 አርሶ አደሮች በመሉ ፓኬጅ ታይ የስንዴ ዝርያ 1.8 ሄክታር ሠርቶ ማሳያ ጎብኝቷል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው በመክፈቻ ንግግራቸው የፕሮግራሙን አላማና ስለሚሠራባቸው ወረዳዎች እና ፕሮጀክቱ በ2011/12 ዓ.ም. አቅዶ እያከናወነ ስላሉ ስራዎች በሰፊው አብራርተዋል፡፡ እስካሁንም በአርሶ አደሩ ማሳ ሰርቶ ማሳያ በወረዳ ደረጃ በታች ጋይንት፣ ላይ ጋይንት፣ እነብሴ ሳር ምድር፣ በወገራ ወረዳዎች የመስክ ምልከታ መደረጉን ገልፀው የወረዳ መዋቅሩም የፕሮግራሙ ሰርቶ ማሳያ መማማሪያ በማድረግ በልምድ ልውውጥ ወደፊት ማስቀጥል እነደሚገባ አሳስበዋል፡፡
 
የጎንደር ግብርና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አስፋው አዛለው አርሶ አደሩን ባወያዩበት ወቅት እንደገለፁት ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ገና የአንድ ዓመት ቆይታ ቢሆንም ወደ ገጠር ቀበሌዎች ወርዶ ስርዓት በመዘርጋት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ ፈጠራ በስልጠና አሳድጓል፡፡ በዚህም አርሶ አደሩን ብቁ አድርጎ ዛሬ በምናየው ደረጃ በተመረጡ ማሳዎች ላይ የዳቦ ስንዴ ሰርቶ ማሳያ ውጤት በተግባር የታየ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ እና ለሌሎችም አርያ የሚሆን ተግባር ነው በማለት የወረዳው መዋቅርም በሰተርቶ ማሳያው የተመለከቱትን የዳቦ ስንዴ ዝርያ ውጤት ለሌሎች አርሶ አደሮች ማስፋት እንዳለባቸው አሳስበዋል ፡፡
 
በውይይቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮች እና በራሱ ማሳ ላይ በተግባር ሰርተው ያሳዩት አቶ አማረ አያሌው በበኩላቸው አንድ የስንዴ ፍሬ የባለሙያ ምክር ተከትሎ፣ በቂ ግብዓት በመጨመር፣ የዕለት ከዕለት እንክብካቤ ታክሎበት በመስመር የተዘራው ስናየው 35፣40 እና 45 እግሮች በማብቀል፤ እያንዳንዱ ዛላም እስከ 72 በማፍራት በጥቅሉ ከአንድ ፍሬ እስከ ሁለት ሺ አምስት መቶ ሃያ የዳቦ ስንዴ ፍሬ እንደሚገኝ በመስክ ምልከታው ማየት ተችሏል ብለዋል፡፡ በቀጣይም በሰርቶ ማሳያ የታየውን የተሻሻለ ዝርያ ወደ አርሶ አደሩ ማሳ ለማዳረስ ቃል ገብተዋል ፡፡
 
በውይይቱ ተጋብዘው የተገኙት የዳባት ወረዳ አርሶ አደር ድንች ከአንድ እግር ወደ 40 ፍሬ በሰርቶ ማሳያ እንደተገኘ እና አሳታፊ የስንዴ መረጣ ከ6 የዘር አይነት የተገኘው ታይ የዘር አይነት የተሻለ እንደሆነ ሲገልፁ በተመሳሳይ ወገራ ወረዳ ብራ ቀበሌ ላይ በዳቦ ስንዴ ሰርቶ ማሳያና የቢራ ገብስ ቅድመ ማስፋፋት ምርቱ የተሻለ እንደሆነ ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡
 
በመጨረሻም በፕሮግራሙ ላይ ሰፊ የመስክ ጉብኝት ከተካሄደ በኋላ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ዲን ዶ/ር ካህሊ ጀንበሬ፣ የወገራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አበበ እና የጎንደር ግብርና ምርምር ዳይሬክተር አቶ አስፋው አዛለው በመሩት መድረክ የጉብኝቱ ውሎ በሰፊው ተዳሶ ከአርሶ አደሮችና ባለሙያዎ ገንቢ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡