የቤነፊት ሪያላይዝ የመስክ ላይ ጉብኝትና ምክክር

                     የተሻሻለ ሰብል ዝርያ በሰርቶ ማሳያ የመስክ ምልከታ ተደረገ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት በታች ጋይንት ወረዳ ቆጥ መንደር የተሻሻለ የስንዴና ገብስ ዝርያ ሰርቶ ማሳያ ላይ የመስክ ላይ ጉብኝትና ምክክር መስከረም 26 አደረገ፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት ማኔጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው በመድረኩ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ እየሰራ ያለው CASCAPE እና ISSD ከተሰኙ ፕሮግራሞች የተገኙ ምርጥ የግብርና ተሞክሮዎችን የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 10 የፕሮግራሙ ወረዳዎች ላይ ማስፋት ነው፡፡ ለዚህም ውጤታማነት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር የሶስት ዓመት ፕሮግራም ምርጥ ተሞክሮዎችን በማላመድ፣ በማረጋገጥ እና በማስፋት የህብረተሰብ ክፍሎችን፣ የድርጅቶችንና የተቋማትን አቅም ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት በደቡብ ጎንደር ጋይንት ወረዳ ቆጥ መንደር ቀበሌ ታይ የተሰኘ የስንዴ እና ትራቪለር የሚባል የቢራ ገብስ ዝርያ የማሳ ላይ ሰርቶ ማሳያ እና የቅድመ ማስፋፋት ስራዎች እንደተሰራ ተናግረዋል፡፡

የፕሮግራሙ ተግባር ተቀብለው እየሰሩ ያሉ አርሶ አደሮች እንዳሉት የቀረበላቸው ዝርያ እስካሁን ከተመለከቱት የተሻለ መሆኑን ተናግረው ለመኖ የሚሰጠው ውጤት አናሳ በመሆኑ ቢሻሻል በማለት አሁንም የግብዓትና የማማከር ድጋፋቸውም ከዚህ በላቀ መልኩ እንዲቀጥል አሳስበዋል ፡፡ ከዚህ ባሻገር በመስክ ምልከታው በታዩ ጠንካራ ጎኖችና ጉድለቶች ላይ ከወረዳ እስከ ክልል ከሚገኙ የፕሮጀክቱ አጋር አካላት ጋር የአካባቢው አርሶ አደሮች በተገኙበት ምክክር ተደርጓል፡፡ በምክክሩም ላይ ከአርሶ አደሮች እና ከግብርና ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንዳሉት 2011-ለ2012 በጀት አመት በተሠሩ የግብርና የተግባር ስራዎች ላይ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በግልፅ ተመልክቶ ደካማውን ደካማ ጠንካራውን ጠንካራ ለማለት እና አዳዲስ አሰራር ፣ ዝርያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ፤ ከቀበሌ ቀበሌ ፣ ከአርሶ አደር ወደ አርሶ አደር ለማስፋፋትና ለአካባቢው ተስማሚ የሚሆነውን ዝርያ ለመምረጥ የመስክ ምልከታው ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል፡፡