የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሀገር አቀፍ ፕላን ኮሚሽን ጋር በመተባበር 4ኛውን የስነ-ህዝብ ልማት ጉባኤ አካሄደ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊና የስነ-ህዝብ ጥናት ትምህርት ክፍል ወጣቱን ለልማት በመጠቀም አስፈላጊነት ላይ የተመሰረተ ለሁለት ቀን የሚቆይ አገር አቀፍ ጉባኤ አካሂዷል። ሀገሪችን ኢትዮጵያ ሆነ አህጉራችን 60 ፐርሰንት የሚሆነው ወጣት እንደሆነና ይህን የህዝብ ፀጋነቱን በመጠቀም ኢንቨስት ማድረግና መጠቀም እንደሚገባ የተናገሩት በመርሀ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ ናቸው። ኢትዮጵያ በወጣት የታደለች ሀገር እንደሆነችና ይህንን ወጣት ኃይል ለልማት በመጠቀም ፀጋ ወይም ጥሩ አጋጣሚ ሲሆን ካልተጠቀምንበት ግን እዳ ሊሆን እንደሚችልና ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ወጣቱ ላይ ኢንቨስት በማድረግ በእድገት ጎዳና እንደተራመዱና በአሁኑ ወቅት ትልቅ የእድገት ማማ ላይ እንደሚገኙና በተለይም ትምህርትን፣ ጤናን፣ ኢኮኖሚን፣ ፈጠራን አጣምረው በመስራታቸው ውጤታማ እንደሆኑና በተቃራኒው ደግሞ ይህን የወጣት ክፍል አቀናጅተው ያልተጠቀሙ ሀገሮች እስከ አሁን ድረስ በድህነት ላይ እንደሚገኙ ነገር ግን ሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነች አህጉራችን አሁን ትኩስ ሀይል እንዳላቸውና ይህን ሀይል ወደ አምራች ፀጋ ለማድረግ ወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ፣ በትክክል መምራትና መጠቀም እንደሚያስፈልግ ምክትል ፕሬዝዳንቷ ገለፀዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ ብዙ ኢንቨስት እንዳደረገችና በዚህም ምክንያት ብዙ ጥቅሞች እንደተገኙበትና ከዚህ በላይ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል። የስነ-ህዝብ ጥሩ አጋጣሚ መጠቀም ለሀገር እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውና የስነ- ተዋልዶ ቁጥጥርን በመጨመር የህጻናትን እድሜ በመቀነስ ከ15 ዓመት በላይ ያሉ ወጣቶችን በትምህርት፣ በጤና፣ በፈጠራ፣ በኢኮኖሚ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ እንዲበለጽጉ በማድረግ ወጣቱን መጠቀምና የሀገሪቱን እድገት ወደ ተሻለ ጎዳና መውሰድ እንደሚቻልና በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ30 አመት እድሜ ክልል በታች የሚሆነው ወጣት 50 ሚሊዮን እንደሚሆንና ይህም ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነ የገለጹት የመርሀ ግብሩ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ዶ/ር አማረ ሰውነት ናቸው። ዶ/ር አማረ አክለውም በዚህ ጉባኤ ላይ ከኮሪያ፣ ከቬትናም፣ ከአሜሪካ፣ ከኬንያ እንዲሁም ከሀገር ውስጥ 13 ዩኒቨርሲቲዎች እና ከሁሉም ክልሎች ተሳታፊ እንደሆኑና ከ40 በላይ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀረቡና የተለያዩ ልምዶች እንደሚገኙበት እንዲሁም የተገኘውን ልምድ በመሰነድ ለሚመለከተው አካል እንደሚሰጡና ለተፈጻሚነቱም ክትትል እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ሀገሪቱ ባለፉት 15 አመታት በሁሉም ዘርፍ ትልቅ ለውጥ እንዳሳየችና የስነ-ህዝብ ስራ የትምህርት፣ የጤናና የኢኮኖሚ ድምር ውጤት እንደሆና አሁን ሀገሪቱ እየተከተለች ያለችው የትምህርት፣ የጤናና የኢኮኖሚ ስራ የስነ-ህዝብ ስራውን እያቀለጠፈው እንደሚገኝ የገለጹት በመርሀ ግብሩ መዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ይናገር ደሴ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት አመታት በመንግስት በተሰራ ስራ በርካታ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሆኑና የዚህ እድል ተጠቃሚ ያልሆኑ ወጣቶች በተለያየ ምክንያት በመኖራቸው ባለፈው አመት እነዚህን ወጣቶች በገጠርም ሆነ በከተማ ተጠቃሚ የሚያደርግ የወጣቶች ፈንድ በማቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝም ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።