የሰላም ምክክር መድረክ

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ‹‹ብዝሃነት መቻቻልና ሰላም ለሀገር ግንባታ›› በሚል መሪ ቃል የግማሽ ቀን የሰላም ምክክር በዋናው ግቢ መሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር እሰይ ከበደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የፆታ፣ የብሄር ወዘተ ብዝሃነት ያለበት የህብረተሰብ አካል እንደሆነ ገልፀው ይህን ብዝሃነት አቻችሎ መኖር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ብዝሃነቱ ደግሞ በአግባቡ ካልተያዘ ወደ ግጭት ይወስደናል በማለት ሁሉም ለአገር ሰላም የበኩሉን በመወጣት የሚጠበቅበትን አገር የመገንባት ስራ በተገቢው እንዲወጣ አሳስበዋል ፡፡

በመርሃ ግብሩ በዶ/ር ሞገስ ደምሴ የስነ ዜጋና ስነምግባር መምህርና ትምህርት ክፍል ሃላፊ ጥናታዊ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን ስለ ሰላም ምንነት፣ አስፈላጊነትና፣ ተግዳሮቶች ዙሪያ ከፍተኛ የሆነ ውይይት ተደርጓል ፡፡ በመጨረሻም ዜጎች በአገራዊ ሰላምና አንድነት ግንባታው ላይ በንቃት እንዲሳተፉና የየድርሻቸውን እንዲወጡ ለማበረታታት እንደዚህ አይነት ምክክሮችና መድረኮች ከፍተኛ አስተዋጾ እንደሚያበረክቱ ተጠቁሟል፡፡

በዕለቱም ከሁሉም ግቢዎች የተሰባሰቡ መምህራንና ተማሪዎች፣ አስተዳደር ሰራተኞችና እና ሌሎች ታድመዋል፡፡