የምረቃ ስነ-ስርዓት ተካሄደ

 

የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ተማሪዎችን አስመረቀ፡፡

በትዕግስት ዳዊት

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የመሬት አስተዳደር ኢንስቲትዩት ስር የሚገኘው የአርክቴክቸር ትምህርት ክፍል ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለሶስተኛ ጊዜ አስመረቀ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መሬት አስተዳደር ዳይሬክተር ዶ/ር በላቸው ይርሳው ለተመራቂ ተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን የቀለም እና የተግባር ትምህርት ወደ ተግባር የሚተረጉሙበት እና ከራሳችው አልፎ ህብረተሰባቸውን የሚያገለግሉበት ጥሩ አጋጣሚ በመሆኑ በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት እንዲሰሩ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ የኪነ ህንጻ ትምህርት ትዕግስት እና ፈጠራ የሚጠይቅ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያሳደጉትን የፈጠራ ክህሎት የበለጠ አጎልብተው እራሳቸውን ጠቅመው ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉበት አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር በላቸው አክለውም የኪነ ህንጻን ሙያ የሚጠይቅ ስራ የሚሰሩ የፌዴራል፣የክልል የግልም ሆነ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ ሃብት እና እውቀት ፈሶባቸው የሰለጠኑ ተመራቂዎችን በአግባቡ ሊጠቀሙባቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂዎች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ እንደተናገሩት የሚገነቡት ከተሞች ብሎም ሀገራት የሚመስሉት የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎችን በመሆኑ ለከተሞች ውበት፣የኑሮ ምቹነት ፣ቀጣይነት፣ወጭ ቆጣቢነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዝዳንቱ ቀጥለውም አሁን ትልቅ የኪነ-ህንፃ ጥበብ የሚታይባቸው የሃገራችን ቅርሶች የመፈራረስ አደጋ የተጋረጠባቸው ጊዜ ሲሆን መታደግ የሚቻለውም በእውቀት እና በጥበብ በመሆኑ ተመራቂዎች ያላቸውን እውቀት እና ጥበብ በተቋርቋሪነት መንፈስ በመጠቀም ከመፍረስ እንዲታደጓቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ፍሬው ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች የኢትዪጵያን ቅርሶች፣መልክምድሮች፣እንስሳት፣እጽዋት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሃብቶች ሌሎች የሌሏቸው መለዮወቻችንን የንድፋቸው ማስጌጫ መጠበቢያ ቅመም በማድረግ እንዲጠቀሙባቸው አሳስበው አለም ከደረሰበት እድገት አንጸርም ዘመኑን የዋጀ ንድፍ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረው ከሁሉም በፊት ግን ህሊናቸውን እና ፈጣሪያቸውን ዳኛ አድርገው የሙያ ስነምግባር በተላበሰ መልኩ እንዲሰሩ በአጽንኦት መክረዋል፡፡ በመጨረሻም ተመራቂዎች በሙያቸው ስኬታማ በመሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲን ብሎም የውድ ሃገራቸውን ስም የበለጠ በበጎ  እንዲታወቁ የበኪላቸውን ያደርጉ ዘንድ አደራ ብለዋል ፡፡

 

በምረቃ በርሃግብሩ የተገኙት አርክቴክት አበበ ይመኑ የረጂም ጊዜ የህይወት ተሞክሯቸውን እና የስራ ልምዳቸውን ለተመራቂዎች ያቀረቡ ሲሆን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትምህርት ክፍል ደረጃ የሚሰሩት የተማሪዎች ፕሮጀክቶች ደረጃቸው ከፍ እንዲል መሰራት እንዳለበት ጠቁመው በተጨማሪም በሙያው ትልቅ ስም ያላቸው አርክቴክቶች ያላቸውን የስራ ልምድ፣ የፈጠራ ችሎታቸውንና ክህሎት ማካፈል የሚችሉበት መርሃግብር ቢዘጋጅ ጥሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አቶ አበበ ይመኑ በመጨረሻም የኪነ ህንጻ ትምህርት በባህሪው የተለየ ክህሎት እና የተለየ ከባቢያዊ ሁኔታ የሚፈልግ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ እና ከ1ኛ-5ኛ ለወጡ ተማሪወች ሽልማት ተስጥቷል፡፡ ከሴቶች ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችው ተማሪ ቃልኪዳን ጥበቡ እንዲሁ ሽልማት የወሰደች ሲሆን ተማሪ በረከት ምትኩ 3.76 በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ የወርቅ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

የዘንድሮው ምርቃት በትምህርት ክፍሉ ሶስተኛው ሲሆን 22 ወንዶች እና 7 ሴቶች በድምሩ 29 ተማሪወች ለምረቃ በቅተዋል፡፡

በእለቱ በተማሪወቹ የተሰሩ  የኪነ ህንጻ ንድፎች አውደ ርዕይ በመርሃ ግብሩ ለተገኙ ተሳታፊወች እና ተመራቂ ቤተሰቦች ተጎብኝተዋል፡፡