የመፅሀፍ ዕርዳታ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ26 ሺ በላይ መፅሀፎች በዕርዳታ አገኘ
==================================
በሙሉጌታ ዘለቀ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር ካደረገው ቡክስ ፎር አፍሪካ ከተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ግንኙነት የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የስነ-ፁሁፍ እና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መፅሀፎችን በዕርዳታ ተረክቧል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አብይ መንክር በመፅሀፍ ርክክቡ ወቅት እንዳሉት መፅሀፎቹ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት በሆኑት ዶ/ር እሰይ ከበደ ከቡክስ ፎር አፍሪካ ጋር በመፃፃፍ የመጡ መሆናቸውን ገልፀው፤ መፅሀፎችን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያስመጣቸው እንጂ ከምርምሩ በተጨማሪ ህብረተሰቡን ከሚያገለግልበት ሂደቶች ውስጥ አንዱ የማህበረሰብ አገልግሎት በመሆኑ በባሕር ዳርና አካባቢዋ ለሚገኙ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች እና ከፍተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈሉ ተናግረዋል፡፡ አቶ አብይ አክለውም እነዚህን መፅሀፎች በማጓጓዝና የትራንዚት ክፍያዎችን በመክፈል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ድረስ እንዲመጣ ያደረጉ ካፒቴን አንተሁነኝ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ አቶ አብይ ካፒቴን አንተሁነኝን አመስግነው ሌሎች ሀገር ወዳድ ባለሀብቶችም የሳቸውን ፈለግ እንዲከተሉ መክረዋል፡፡
 
ቡክስ ፎር አፍሪካ የተሰኘው ድርጅት የተለያዩ መፅሀፎችን አሜሪካን ሀገር ካሉ ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት እያሰባሰበ ለተለያዩ አፍሪካ ሀገራት በእርዳታ የሚያበረክት ግብረ-ሰናይ ድርጅት ነው፡፡ መፅሀፎች ከ1ኛ - 4ኛ ክፍል፣ከ5ኛ- 8ኛ፣ ከ9ኛ-12ኛ እና ለጎልማሶች ትምህርት የሚያገለግሉ ከ26ሺህ በላይ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የስነ-ፁሁፍ እና የማህበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡