የመርከብ ባለሙያዎች ተመረቁ

ዩኒቨርሲቲው 43 የባህር መርከብ ባለሙያዎችን አስመረቀ፡፡
፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡፡
በሙሉጌታ፡ዘለቀ
 
የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሜካኒካል እና በኤሌክትሪካል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙ ተማሪዎችን ተቀብሎ በባህር ላይ በመካኒካል እና በኤሌክትሪካል ምህንድስና ኦፊሰርነት ለስድስት እና ለስምንት ወር ተኩል ያሰለጠናቸውን 43 ባለሙያዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡
 
ተቋሙ የመርከብ ባለሙያዎቸን ለአለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ለወጣቶች የስራ እድልና ለሀገሪቱም የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ ብቸኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ማሪታይም አካዳሚ በሀገራችን ኢትዮጵያ ብሎም በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛው የመርከብ ባለሙያዎች ማሰልጠኛ አካዳሚ መሆኑና የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ የዚህ ተቋም መገኛ መሆኑ ከሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አንፃር ሲታይ በአውሮፓና በሌሎችም የአለማችን አህጉራት ስሙ ከአካዳሚው ጋር በተያያዘ የታወቀና ለወደፊቱም በምርምርም ሆነ በማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ጠንክሮ መስራት እንዳለበት ተነግሯል፡፡
የምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ\ር ፍሬው ተገኘ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ በየጊዜው የባህር ላይ ባለሙያዎችን ከማፍራት ባሻገር ሰልጣኞችም (cadets) ለሌሎችም የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች አርአያ መሆን የሚችሉ በዲስፕሊን የታነጹ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ የእለቱ ተመራቂዎች ለስራ በሚሄዱበት ሀገር እንደ አንድ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብ አምባሳደር በመሆን የሀገራችን ገፅታ በበጎ መገንባትና ማስተዋወቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
 
ዶ/ር ፍሬው አክለውም የእለቱን ምርቃት ከእስካሁኑ የሚለየው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ\ር አብይ አህመድ በአለም አቅፍ ደረጃ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆን የኢትዮጵያ ሀገራችንን ስም እና ህዝቦቿን በበጎ ጎን ለአለም ያስጠሩበት ቀን መሆኑ ነው ብለዋል፡፡ በመጨረሻም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ለተመራቂዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች አስተላልፈው ለዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች እና በትምህርታቸው አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት እና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ የስልጠና አስተዳደርና የሰው ሀብት ማኔጄር አቶ ዘላለም ተፈሪ እንዳሉት አካዳሚው ተማሪዎችን ሲያስመርቅ ይህ ለ18ኛ ጊዜ ሲሆን የዛሬ ተመራቂዎቸ ቁጥራቸው አርባ ሦስት መሆናቸው ገልፀው ተማሪዎች ወደ አካዳሚው ሲገቡ ከትምህርት ማስረጃቸው በተጨማሪ ጤንነታቸው በህክምና የተረጋገጠ እና ዕድሜያቸውም ከ26 አመት በታች የሆኑ ወንዶች እንደሆኑ ገልፀዋል፡፡ ስልጠናውን ጨርሰው የሚመረቁ ተማሪዎችም በአለም አቀፍ የመርከብ ድርጅቶች ተቀጥረው የመስራት ዕድል ያላቸው ሲሆን ዜጎችን በሙያ እያሰለጠኑ ለባለሙያዎች የውጭ የስራ ዕድል መፈጠሩ እንደ በጎ ተግባር ሊታይ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በእለቱም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማሪታይም አካዳሚ እስካሁን ከ1500 በላይ የመርከብ ላይ ባለሙያዎችን እንዳስመረቀ ተጠቅሷል፡፡