ውይይት ከሜሪላድ እና ሂብሪው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሜሪላድ ዩኒቨርሲቲና ሂብሪው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ውይይት አካሄደ።

 በትዕግስት ዳዊት

በሶስትዮሽ የውይይት መርሀ ግብሩ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የዩኒቨርሲቲያቸውን ታሪክ፣ራዕይ፣እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው ያለበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለተሳታፊዎች ገለፃ አድርገዋል፡፡ በውይይቱም  ከሁለቱ የታወቁ  ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን የሚቀሰመውን ጠቃሚ ልምድና፣ እውቀት የዩኒቨርሲቲውን ራዕይ ለማሳካት እንደሚጠቅም ፕሬዚዳንቱ እምነታቸውን ገልፀዋል።

ከሜሪላንድ እና ሂብሪው ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ፕሮፌሰሮች የየዩኒቨርሲቲያቸውን ተሞክሮ፣  እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች ያቀረቡ ሲሆን ምሁራኑ አክለውም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲም የተቋማቶቻቸውን የምርምር፣ የህትመት፣ የቴክኖሎጂና መሰል ልምዶችን በመውሰድ እንዲጠቀምበት ጠቁመዋል፡፡ ወደፊትም ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በተለያዩ መስኮች አብረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሲቪልና ውሃ ትምህርት ክፍል መምህር፣ረዳት ተመራማሪ እና የብሉ ናይል ውሃ ተቋም ዳይሬክተር ዶ/ር ማማሩ አያሌው በምግብ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሁም ጤናና መሰል ጉዳዮች ላይ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ከመጡት ምሁራን ጋር ሰፊ ውይይት በማድረጋችው አለም አቀፋዊ እውቅና ያላቸው ተቋማት ያላቸውን ተሞክሮ፣ እና ትልቅ ልምድ መጋራት ተችሏል ብለዋል፡፡ ወደፊትም በጋራ ትልመ ጥናት በማዘጋጀት እና በአጭር ጊዜ ወደ ትግበራ በመምጣት በስነ-ምግብ፣ ጤናና ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ስራ እንደሚሰሩ ዳይሬክተሩ እምነታቸውን ተናግረዋል።

በውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው የውሀ፣ ምግብና ህብረተሰብ ጤና  ምሁራን እንዲሁም ከሁለቱ የውጭ ተቋማት የመጡ ምሁራን ልምዳቸውን፣ተሞክሯቸውንና ይጠቅማሉ ያሏቸውን የምርምር ጥናቶች (ወረቀቶች ) ያቀረቡ ሲሆን ከተሳታፊዎች ጋርም ሰፊና ውጤታማ ውይይት ተደርጓል፡፡ ተሳታፊ ምሁራኑ በዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ ግቢዎች የሚገኙ ፋርሞችን እንዲሁም  ፈሳሽ እና ጠጣር ቆሻሻ ማስወገጃ ስራዎችንና የተለያዩ ክንውኖችን ጎብኝተዋል።