ወገን ለወገን

ለወገን ደራሽ ወገን ነው፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 05 በ28/06/11ዓ.ም ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት አካባቢ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለተጎዱ ወገኖቻችን የብርድ ልብስ እና የመኝታ ፍራሾች ድጋፍ አደረገ፡፡

ይህ ድጋፍ የተደረገውም  በቃጠሎው  ሙሉ ለሙሉ ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖች  ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ በቃጠሎው ምክኒያት ንብረታቸውን ላጡ ወገኖች ሃዘናቸውን ገልጠው በሰው ህይወት ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱ የሚያጽናና ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ንብረቱ በሀገራችንና በከተማችን ሰላምና የተሻለ አስተዳደር እስካለ ድረስ ተሰርቶ የሚመጣ ስለሆነ በደረሰው አደጋ ሳይደናገጡ የወደፊት ህይወታቸውን ከተለያዩ አካላት ከሚያገኙት ድጋፍ በተጨማሪ ጠንካራ መንፈስ በማዳበር ሰርተው ለመለወጥ ቆርጠው መነሳት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲውም በክልሉ እና በአገር አቀፍ ደረጃ በሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች አቅሙ የሚችለውን ሁሉ ከማድረግም ባለፈ ለዘለቄታው በእውቀትና በምርምር የታገዘ የአደጋ መከላለከልና ዘላቂ ልማት ስራ በየዘርፉ ባለሞያዎችን እያሰለጠነ መሆኑን ገልጠዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ሙሉቀን አየሁ በበኩላቸው በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት በደረሰው ያልታሰበ ድንገተኛ አደጋ ማዘናቸውን ገልጠው ከተለያዩ አካላት ልዩ ልዩ ድጋፍ ለተጎጅዎች እየተደረገ መሆኑን በመጠቆም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም ላደረገው ፈጣን የፍራሽና የብርድ ልብስ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በወቅቱም ዩኒቨርሲቲው 500 የሚደርስ ብርድልብስና 500 ፍራሽ ለከንቲባውና ለሚመለከታቸው የክፍለ ከተማ ተወካዮች አስረክቧል፡፡