አፈር አልባ የእንስሳት መኖን ማልማት ስለሚቻልበት ሁኔታ ተግባር ተኮር ስልጠና ተሰጠ

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት ከአፍሪካ ሀገሮች የተሻለ ደረጃ ላይ ብትገኝም በእንስሳት መኖ እጥረት ምክንያት ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያገኘች እንዳልሆነ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ችግር አኳያ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የተለያዩ የንጥረ ነገር ውህዶችን በመጠቀም የፅንሰ-ሃሳብና የተግባር ስልጠና ለተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በግብርናና አካባቢ ሣይንስ ኮሌጅ ግቢ ቤተ-ሙከራ ለ7 ተከታታይ ቀናት ሰጥቷል፡፡

የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶ/ር የሻምበል መኩሪያው ቴክኖሎጅን በመጠቀም ማንኛውም ማህበረሰብ በቀላሉ አረንጓዴ የእንስሳት መኖ በአጭር ጊዜ፣ በአነስተኛ ጉልበትና ውሃ በርካታ የእንስሳት መኖ በማዘጋጀት መጠቀም የሚቻልበትን ዘዴ ለማሳወቅ ስልጠናው ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለቴክኖሎጂው ዋና ግብዓት የሆነውን ውህድ በዩኒቨርሲቲው የኬሚስትሪ ት/ክፍል ሙሁራን ተሰርቶ የቀረበ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከGIZ የእንስሳት ሃብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ የመጡት አሰልጣኝ አቶ ኃይለየሱስ አባተ የቴክኖሎጂውን ግኝትና አዋጭነት ሲገለፁ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው፣ በተለይ ዝናብ አጠርና ድርቅ በሚያጠቃቸው ቦታዎች አካባቢ በስፋት መሰራት እንደሚቻል፣ በ7 ቀናት ውስጥ ከ25-30 ሴንቲ ሜትር ርዝመት ያለው አረንጓዴ መኖ ማድረስ እንደሚቻል እንዲሁም ከ 1 ኪሎ ግራም ገብስ ከ6-10 ኪሎ ግራም የሚመዝን የእንስሳት መኖ በቀላሉ ማግኘት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ አያይዘውም መኖው በተለይ ለእንቁላል ጣይ ዶሮዎች የንጥረ ነገሩ ውህድ ከፍተኛ ፕሮቲን ስላለው በርካታ እንቁላል የመጣል አቅማቸውን እንደሚያጐለብትና ስልጠናው ከሙከራ እስከ ትግበራ መሰጠቱን አስገንዝበዋል፡፡ ሰልጣኞች በባሕር ደር ከተማ የተደራጁ ሥራ አጥ ወጣቶች፣ የኮሌጁ የእንስሳት እርባታ ሠራተኞች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲውን መምህራንና የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ሲሆኑ ከስልጠናው ከፍተኛ ግንዛቤ እንደጨበጡና በቆይታቸው መኖው ለእንስሳት መቅረብ መቻሉን ብሎም የኮሌጁ ላሞችና በጐች ሲመገቡት ማስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡