ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት

ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮጀክት የተሻሻለ የድንች ዘር  ሰርቶ ማሳያ የመስክ ምልከታ አካሄደ ፡፡

---------------------------------------------------------------------------------

በሙሉጌታ ዘለቀ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት በጋይንት ወረዳ አቃቤት ቀበሌ የተሻሻለ የድንች ዝርያን ሰርቶ ማሳያ የመስክ ላይ ጉብኝትና ምክክር ባለድርሻ አካላት ፣ የወረዳው ኃላፊዎችና የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የመስክ ጉብኝቱን በንግግር የከፈቱት የላይ ጋይንት ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ታረቀኝ ዮሴፍ ሲሆኑ ቤነፊት ሪያላይዝ ፕሮግራም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር  ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን የወረዳውን አርሶአደር ህይወት ለመቀየር በተለይ የተሸሻለ የድንች ዝርያዎችን በማቅረብና ግብዓቶችን በማሟላት እንዲሁም በሙያው የምክር አገልግሎት በመስጠት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን በማስቀጠልና አርሶአደሩም ቢሆን  ያገኘውን መልካም ተሞክሮ በማስፋትና የግብዓት አጠቃቀምን በማዘመን የግብርና ባለሙያዎች የሚነግሯቸውን ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ ስራ መሰራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡  

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው እንዳሉት ፕሮግራሙ ዋና አላማው ምርጥ ተሞክሮዎችን በማልማት፣ በማላመድ፣ በማረጋገጥ፣ ሰርቶ በማሳየትና በማስፋት ብሎም የተቋማትን አቅም በመገንባት በክልላችን ላሉ የምግብ ዋስትናቸውን ላረጋገጡ የህብረተሰብ ክፍሎች አለኝታ ሆኖ መገኘት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ  ላይ ጋይንት ወረዳ ላይ የድንችና የጓሮ አትክልት ሰርቶ ማሳያ፣ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር የሚያስችል የተሸሻለ የከሰል ማክሰያ ቴክኖሎጂ ሰርቶማሳያ እና ጥልቅ የምርምር ጥናት እንዲተገበር በማድረጉ የፕሮጀክቱን ጠንካራነት ይበልጥ እንዲያጎላው አድርጓል ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እንደሌሎች ፕሮጀክቶች የማብቂያ ጊዜ ያለው መሆኑን ገልፀው፤ በክልላችን ያሉ በምግብ እህል ራሳቸውን ያልቻሉ አርሶአደሮች ላይ በይበልጥ ትኩርት አድርጎ እንደሚሰራና ገበሬው በፕሮጀክቱ በኩል የሚቀርቡ የተሸሻሉ ዘሮችን እና ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ለወደፊት ፕሮጀክቱ ባይኖር እንኳን እራሱን ችሎ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ከራሱም አልፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን እንዳለበት ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

በመስክ ምልከታው ላይ የላይ ጋይንት ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው ቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ከመጣ አጭር ጊዜው ሲሆን በወረዳቸው ላይ እየሰራ ያለው ስራ ግን አመርቂ መሆኑን መስክረዋል፡፡  ኃላፊው አክውም ወረዳው በድንች ፣ በቢራ ገብስና በስንዴ ምርት በጣም የታወቀ በመሆኑ ፕሮጅከቱ ለቀሪዎችም ትክረት ሰጥቶ ቢሰራ አርሶአደሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሴፍትኔት ፕሮግራም በመላቀቅ እራሱን የሚችልበትና ምርቱንም ለገበያ የሚያቀርብበት ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ተካተው እየሰሩ ያሉ አርሶአሮች እንዳሉት ይህ #የበለጠ; ድንች ምርጥ ዘር ከመጣ ጀምሮ የድንች ምርት በበቂ ሁኔታ እያገኙ መሆኑን ተናግረው አሁንም ከዚህ የተሸለ ዘር ፕሮጀክቱ እንዲያመጣላቸውና ተከታታይ የግብዓትና የማማከር ድጋፋቸውም ከዚህ በላቀ መልኩ እንዲቀጥል  ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም ከመስክ ምልከታ በኋላ በአርሶአደሩ እና በድንች ዝርያው ላይ በታዩ ጠንካራ ጎኖችና ጉድለቶች ላይ ከፕሮጀክቱ አጋር አካላት፣ ከወረዳ ባለስልጣናትና፣ ከግብርና ባለሙያዎች ጋር የአካባቢው አርሶአደሮች  በተገኙበት ምክክር ተደርጓል፡፡ በምክክሩም ላይ ከአርሶአደሮች እና ከግብርና ባለሙያዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የቤነፊት ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ፕሮጀክት ማናጀር የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው እና የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ማብራሪያ ተሰጥተዋል፡፡