ባሕር ዳር እንደቤቴ ፕሮጀክት

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለ’’ባሕር ዳር እንደቤቴ‘’ ፕሮጀክት መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ ላበረከቱ እውቅና ሰጠ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወደተቋሙ በሚመጡ ተማሪዎችና በባሕር ዳር ከተማና አካባቢዋ ነዋሪዎች መካከል ቤተሰባዊ ግንኙነት ለመፍጠር በነደፈው ’’ባሕር ዳር እንደቤቴ‘’ ፕሮጀክት ከፍተኛ ተሳትፎ ለነበራቸው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና ለከተማዋ ማህበረሰብ አካላት እውቅና ሰጠ፡፡

በዚህ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ (ፔዳ) በተዘጋጀው የእውቅና ፕሮግራም ላይ በፕሮጀክቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበራቸው አስተባባሪ የዩኒቨርሲቲው መምህራን፣ የባሕር ዳር ከተማ ወጣቶችና ማህበራት የበጎ ተግባር የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በዚህ የእውቅና ፕሮግራም ላይ ስለፕሮጀክቱ ማብራሪያ የሰጡትና ከዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ፕሮጀክቱን በበላይነት የመሩት የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ቃለወንጌል ምናለ እንደተናገሩት ይህ ፕሮጀክት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም በመልካም ተሞክሮነት ይወሰዳል ተብሎ እውቅና የተሰጠው በጎ ተግባር መሆኑ ለዩኒቨርሲቲውና ለባሕር ዳር ከተማ ኩራት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ለወደፊቱም ፕሮጀክቱ ይበልጥ እንዲሰራበት ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ለፕሮጀክቱ መሳካት ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸውን አካላት ለማመስገን በተዘጋጀው የእራትና የእውቅና ፕሮግራም ላይ ለተሳታፊዎቹ የምስክር ወረቀት የሰጡት የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ለዚህ ፕሮጀክት መሳካት ጠንክረው የሰሩትን የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አካላትና የባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን አመስግነው በዚህ ፕሮጀክት እስካለሁን የተመዘገበው አመርቂ ውጤት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነና በቀጣይም ተቋሙ ከማህበረሰቡ ጋር በተሻለ ጥምረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል፡፡