በጎርፍ አደጋ ለተጠቁ ድጋፍ ተደረገ

         በጎርፍ አደጋ ለተጠቁ አርሶ አደሮች የገንዘብና አልባሳት ድጋፍ ተደረገ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግሽ አባይ ግቢ ፈቃደኛ የሆኑ ሠራተኞች እና ከዩንቨርሲቲው ጥበበ ጊዮን መንደር ቁጥር 2 የተሰባሰቡ ነዋሪዎች በጎርፍ አደጋ ለተጠቁ የፎገራ ወረዳ አርሶ አደሮች የሚውል የገንዘብና የአልባሳት ድጋፍ አደረጉ፡፡

በስነ ስርዓቱ በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን የፎገራ ወረዳ አስተዳደር የተግባቦት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሙሉነህ አበበ ድጋፉን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት በወረዳው 6 ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በውሃ የተያዙ ሲሆን ቀበሌዎችም ገጠራ ፣ ሻጋ ፣ ኮኪት ፣ ሸና ፣ ቅድስተ ሀና ፣ አባ ኮኪት ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡  ኃላፊው በመቀጠልም በዞኑ በከፊል በውሃ የተያዙት ቀበሌዎች ቋራ አቦ ፣ ቋሪቴ ፣ ወረታ ዙሪያ እና ተዋሃ ዘቀር መሆናቸውን ገልፀዋል ፡፡

ከዩንቨርስቲው ሰራተኞች በኩል በግል ተነሳሽነት በመንቀሳቀስ ይህን አርአያነት ያለው ተግባር ያከናወኑት አቶ ተገኘ መንክር የትራንስፖርት ክፍል ሀላፊ፣ አቶ ገነቱ አንዷለም የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር፣ አቶ ፈለገጊዮን ዘገየ የማኔጅንግ ዳይሬክተር፣ አቶ መሀመድ ዳውድ የህግ መምህር ናቸው፡፡ በእለቱም በእነዚህ በጎ አሳቢ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች የተሰበሰበ በጥሬ ገንዘብ ብር 25920 (ሃያ አምስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሃያ ብር)  ፣ 32 ፍራሽ ፣ 16 ማዳበሪያ እና የተለያዩ አልባሳት ለተጎጂዎች ተበርክቷል ፡፡