በኔፊት-ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ክልላዊ ጉባኤ

  በኔፊት-ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ክልላዊ የባለ ድርሻ አካላት ጉባኤ አካሄደ

በኔፊት-ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ክልላዊ የባለ ድርሻ አካላት ዓመታዊ ጉባኤውን በባሕር ዳር ከተማ ህዳር 24,2012 ዓ.ም.  አካሄደ፡፡

ጉባኤውን በይፋ የከፈቱት በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ግብርና ቢሮ ም/ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን አሰፋ ሲሆኑ ግብርና ብቻውን ሊደርስባቸው ወይም ሊከውናቸው ባልቻሉ ተግባራት ላይ የበኔፊት-ሪያላይዝ ፕሮጀክት ወደ አርሶ አደሩ በመውረድ በጊዜዊነት/በቋሚነት የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ 10 ወረዳዎች ውጤታማ እንቅስቃሴ አድርጓል ብለዋል፡፡ የተደረገው የማላመድ፣ የሰርቶ ማሳያ እና የቅድመ ማስፋት እንዲሁም የአቅም ግንባታ እና የድጋፍ ክትትል ስራ ውጤታማ በመሆኑ ቢሮአቸውም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከበሽታ ነፃ የሆኑ ዝርያዎችን በማቅረቡ ሂደት ከአጋር አካላት ጋር ተቀናጀተን በስፋት የምንሰራበት ይሆናል ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ዪኒቨርስቲ በኔፊት-ሪያላይዝ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አልማዝ ጊዜው በበኩላቸው ባለፋው አንድ አመት የነበሩ ስራዎችንና ተግዳሮቶች አቅርበዋል፡፡ ከተከናወኑ ተግባራትም አሳታፊ የተሻሻለ የዳቦ የስንዴ ዘር መረጣ፣የማሽላ፣የበቆሎ እና የጤፍ የማላመድ፣የቢራ ገብስ እና የቦሎቄ ቅድመ ማስፋት፣ የድንች፣ የፓፓያ፣ የስንዴ፣ የከብት መኖ፣ የጓሮ አትክልት ሰርቶ ማሳያ  እና የ1000 ብር የስንዴ ፓኬጅ ስራዎች ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡ በተመረጡ አስር ወረደዎች በስርዓተ ምግብ አመጋገብና  በልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎቸ፤ እንዲሁም በአጠቃላይ በተሰሩ ስራዎች ላይ የመስክ ምልከታ መደረጉን በምሳሌ አውስተዋል፡፡ አክለውም በኔፊት-ሪያላይዝ  ቀጣይነት እንዲኖረው እና ከታች ያለው የገጠሩ ህብረተሰብ ተጠቃሚ እንዲሆን ከላይ ያለን ባለሙያዎች ተባብረንና ተናበን በመስራት የአርሶ አደሩን ኑሮ የተሻለ መድረግ ይቻለል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም በፕሮግራሙ ለተመረጡ የምግብ ዋስትናቸውን ላረጋገጡ የሴፍቲኔት ወረዳ አርሶ አደሮች እንዲሁም የህብረተሰቡን፣ የተቋምና የድርጅቶችን አቅም በማሳደግ አዳዲስ ግኝቶችን ማረጋገጥ፣ ማላመድና ቅድመ-ማስፋፋት ስራዎችን በቀጣዩ አንድ አመት አጠናክሮ ለመቀጠል የሚያስችሉ መነሻ እቅዶችን አቅርበዋል:: ተሳታፊዎችም ለዕቅዱ ግብዓት የሚሆኑ ፍሬ ሃሳቦችን ከወረዳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር አቅርበዋል፡፡

በመቀጠል የአስሩም ወረዳ የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ምክትል ኃላፊዎች በየወረዳቸዉ በ2011/12  የምርት አመት በፕሮግራሙ የተከናወኑ ስራዎችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ ተግባራትን አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም ከምርምር፣ ከዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም ከኤፍ ኤች ኢትዮጵያ እና ከአግሪ ስርቪስ የመጡ ተሳታፊዎች  የምግብ ዋስትናቸውን ላላረጋገጡ ወረዳዎች ያላቸዉን ቴክኖሎጂዎች እና ስራዎች አቅርበዋል፡፡ 

በጉባኤው የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው የተገኙ ሲሆን የፕሮግራሙን አንድ ዓመት ውጤታማ ቆይታ አውስተው አዳዲስ ቴክኖሎጅዎችን ከውጭ ወደ አገር ስናመጣ ለአካባቢው ተስማሚ እና አስፈላጊ መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ አክለውም ፕሮጀክቱ እንደ ማሳያ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ በሚቋረጥበት ጊዜ ስራውን ማስቀጠል ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የማጠቃለያውን ንግግር ያደረጉት የአብክመ ምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አማረ ክንዴ ሲሆኑ የምግብ ዋስትናቸውን ባላረጋገጡ ወረዳዎች ላይ የሚሰራው ስራ ይበል የሚያሰኝና የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመው ወረዳዎች በያዙት ዕቅድ መሰረት በኔፊት-ሪያላይዝ በሚሰራባቸው ጉዳዮች ላይ የካፒታል በጀት ተጠቅመው መስራት እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡