ስርዓተ-ምግብ ተኮር ስልጠና ተሰጠ

                             በስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤነፊት-ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም ለታቀፉ ዳባት ፣ ወገራ ፣ ስማዳ ፣ ታች ጋይንት ፣ ላይ ጋይንት ፣ እብናት ፣ሊቦ ከምከም ፣ እነብሴ ሳር ምድር ፣ ጎንቻ ሲሶ እነሴና ሸበል በረንታ ወረዳዎች ለሚገኙ የግብርና ጽ/ቤት ባለሙያዎች በስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና በወረታ ከተማ ከሐምሌ 01 እስከ 04/2011 ዓ.ም. ተሰጠ ፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የኤክስቴንሽን ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን አቢቶ በመርሃ ግብሩ ተገኝተው እንደተናገሩት በፕሮግራሙ የተመረጡ 10 ወረዳዎች የምግብ ዋስትና እጥረት ያለባቸው በመሆኑ ይህ ስልጠና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የመቀንጨር አደጋ የተጋረጠባቸውን ህፃናት ለመታደግ እንዲቻል አንድ እርምጃ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ ሃላፊው አክውም የምግብ ዋስትና እጥረትንና  የመቀንጨር አደጋን ለመከላከል ለጉዳዩ ባለቤት ሆኖ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል ፡፡

በነፊት-ሪያላይዝ (BENEFIT REALISE) ፕሮግራም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ማኔጀር ዶ/ር አልማዝ ጊዜው የፕሮግራሙን አላማና ስለሚሠራባቸው ወረዳዎች እና በ2011/12 አቅዶ እየሠራባቸው ስላሉ ስራዎች በመግለፅ ከግብርና ምርምር እና ባህር ዳር ፣ ጎንደር ፣ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አብረው እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡ ሀላፊዋ አክለውም ፕሮግራሙ የድርጅቶችን እና የተቋማትን አቅም በማጎልበት ምርጥ ተሞክሮ ማስፋት ፣ ምርጥ ዘር ማስተዋወቅ ( ከምርምር እና ግብርና ጋር በመተባበር ) ፣ የአሰራር ማነቆዎችን በማስወገድ በምርምር ያተኮረ አዳዲስ የአሰራር ስልቶችን መቀየስ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል ፡፡

ስልጠናው የስርዓተ-ምግብ መሰረታዊ ፅንሰ ሐሳብ፣ የግብርናና የስርዓተ-ምግብ ትስስር፣ የእፅዋት እና የእንስሳት ተዋፅኦ ምግቦችና  የስርዓተ-ምግብ ተኮር ግብርና አተገባበር፣ የውሃ ንፅህና አጠባበቅና ስርዓተ-ምግብ፣ ስርዓተ-ፆታና ስርዓተ-ምግብ፣ ማህበራዊ የባህሪይ ለውጥ መስተጋብር፣ የአጋር አካላት ቅንጅት ለስርዓተ-ምግብ መሻሻል በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በስልጠናው ከየወረዳዎቹ ግብርና ጽ/ቤት የሰብል ልማት፣ የኤክስቴሽን ኮሙኒኬሽን፣ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የስርዓተ-ምግብ ባለሙያዎች እና ቡድን መሪዎች የሆኑ 53 ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል ፡፡

በስልጠናው በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ መምህር እና የስርዓተ-ምግብ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደግነት ተፈራና አቶ ግርማ ነጋ እንዲሁም በቤነፊት-ሪያላይዝ (BENEFIT-REALISE) ፕሮግራም የአቅም ግንባታ ባለሙያ አቶ አሳዮ ተሠማ በአሰልጣኝነት ተሳትፈውበታል ፡፡

በመጨረሻም ከክልሉ ግብርና ቢሮ የስርዓተ-ምግብ ባለሙያዎች በተገኙበት  የስርዓተ-ምግብ  ተኮር ግብርና በሚል ርዕስ  የተሰጠውን የአሰልጣኞች ስልጠና በሚገባ ተከታትለው ላጠናቀቁ  ተሳታፊዎች በፕሮጀክት ሀላፊዋ ዶ/ር አልማዝ ጊዜው አማካኝነት የምስክር ወረቀት ተበርክቷል ፡፡