ለአርሶ አደሮችና ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ

ለአርሶ አደሮችና ለባለሙያዎች ስልጠና ተሰጠ።
በትዕግስት ዳዊት
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለ222 አርሶ አደሮች የቡና አመራረትና ድህረ ምርት አያያዝ የንድፈ ሀሳብ እንዲሁም የተግባር ስልጠና ተሰጥቷል። የዚህን ስልጠና ማንዋል ያዘጋጁት የዩኒቨርሲቲው ምሁራን
1. ዶ/ር ምናለሸዋ አጥላባቸው -የኬሚካዊ ይዘታቸውን(ጣዕማቸውን) ላይ 
2. ዶ/ር መልካሙ አለማየሁ - በድህረ ምርት እንዲሁም ምርት አያያዝ ላይ
3. ዶ/ር ዳንኤል አያሌው - ለቡና ልማት ተስማሚ የሆኑ ቦታዎችን መረጣና ካርታ ዝግጅት ላይ 
4. ዶ/ር ብዙአየሁ ቀሪሰው - የቡና ዘረመል ልየታው ላይ በመሳተፍ 
የስልጠናው ዋና ይዘት የቡና አመራረትና ድህረ ምርት አያያዝ ላይ ሲሆን ስልጠናው የአማራ ክልል የቡና ምርት፣ ጥራትና የገበያ ድርሻ ለማሳደግ ያለመ ነው፡፡ ስልጠናውን ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያቀረበው ሲሆን አርሶ አደሮችና የዘርፉ ባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት በአማራ ክልል ያሉ ቡና አምራቾች ከዘርፉ የሚጠቀሙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ያለመ ነው።
የስልጠናው ይዘት በዋናነት የሚያጠነጥነው የቡና ልማት አስፈላጊነትና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፣ በአለም ላይ በሚታወቁ ዋና ዋና የቡን ዝርያዎች ላይ፣ ለቡና ተክል ልማት ተስማሚ ሁኔታዎችን የመለየት፣ የቡና ዘር አመራረጥና ዝግጅት፣ የቡና ችግኝ ጣቢያ አመሰራረት እና ችግኝ ዝግጅት፣ የቡና ችግኝ ተከላ እና ማሳ አዘገጃጀት፣ በቡና ማሳ ውስጥ የሚደረጉ አጠቃላይ እንክብካቤዎች እንዲሁም የቡና ምርት አሰባሰብ፣ ዝግጅትና ጥራት አጠባበቅ በሚሉት እና በመሳሰሉት ጭብጦች ላይ ያጠነጠኑ ነበሩ።
ዶ/ር መልካሙ አለማየሁ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ የድህረ ምርት አያያዝ መምህር እና ተመራማሪ ሲሆኑ ለአርሶ አደሮችና ባለሙያዎች እንዳሉት በስልጠናው በአማራ ክልል የሚገኙ 222 ቡና አብቃይ አርሶአደሮች እና የዘርፉ ባለሙያወች የተሳተፉበት ሲሆን ሰልጣኞችም ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ላልሰለጠኑ አርሶ አደሮች እና የአካባቢያቸው ነዋሪዎች እንዲያሰለጥኑ በማሰብ ሲሆን ለሰልጣኞችም የስልጠናው ማንዋል ተሰጥቷቸው ብለዋል፡፡ ዶ/ር መልካሙ አክለውም ሰልጣኞች አሰልጣኞች እንዲሆኑ በማድረግ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች ከዘርፉ ተጠቃሚ የሚሆኑበት እንዲሁም የአካባቢያቸው ቡና እንደየሀገሩ ስምና እንደጥራት አይነት/ብራንድ/ የምርት መለያ ስያሜ ተሰጥቶት ልክ እንደሌሎች የሀገራችን ክፍል ቡናዎች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን እንዲያገኙና እንዲታወቁ ይሰራል ብለዋል ።
ስልጣኞች በጎ ፈቃደኛ በሆነች ሴት አርሶ አደር ጓሮ በሚገኙ ቡናዎች ላይ የተግባር ልምምድ ያደረጉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ለድህረ ምርት አያያዝ የሚረዳ አልጋ በተግባር በመስራትና በማሳየት ሰልጣኞችም ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በተግባር ያዩትን በመተግበርና ተጠቃሚ በመሆን ኑሯቸውን እንዲቀይሩ ዶ/ር መልካሙ አሳስበዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ አርሶ አደሮችም ስልጠናውን በመውሰዳቸው ጠቃሚ መረጃ በማግኘታቸው ምርታቸውን ለማሳደግ እንዲሁም ከቡና ልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።