ለተፈናቃዮች ድጋፍ ተደረገ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለተፈናቃዮች የተለያዩ ድጋፎችን አደረገ።

በትእግስት ዳዊት

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአማራ ክልል ሰው ሰራሽ በሆነ ምክንያት ለተፈናቀሉና በከፍተኛ ችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች ድጋፍ አደረገ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከቀያቸው በመፈናቀላቸው ምክንያት የእለት ጉርስ፣ መጠለያና አልባሳት ለሌላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ቀደም ሲል ብር 2000000.00/ 2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን አሁን ደግሞ የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ኮሚቴ በማዋቀር የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ፋሽን ዲዛይን ኢንስቲትዩት ብር 600000.00 /ስድስት መቶ ሽህ ብር/ የሚገመት አልባሳትና ጫማዎች፣ በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪነት ዩኒቨርሲቲው ለምርምር ከመንግስት ከወሰደው 50 ሄክታር  መሬት ላይ የበቀለ 650 ኩንታል በቆሎ፣ 32 ኩንታል ጤፍ፣ እና 30 ኩንታል ስንዴ በድምሩ ግምቱ ብር1000000.00/1ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 710 ኩንታል የቀለብ እህል የተሰጠ ሲሆን፤ ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብም ብር 457232.00 /አራት መቶ አምሳ ሰባት ሽህ ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለት ብር/ በጥሬ ገንዘብ ለተመሳሳይ ዓላማ ተሰብስቧል፡፡ በአጠቃላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ 2057232.00 /ሁለት ሚሊዮን አምሳ ሰባት ሽህ ሁለት መቶ ሰላሳ ሁለት ብር/ ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አማረ ክንዴ በሃገራችን በምዕራብና ማእከላዊ ጎንደር፣ ከአጎራባቾች አሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በክልሉ ተፈናቅለው  እንዳሉና በ20 ጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ አዝማድ ተጠልለው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ወደነበሩበት አካባቢ ለመመለስና ለማቋቋም የተለያዩ የገቢ ማሰባሰብያ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

አቶ አማረ እስካሁን የተለያዩ እርዳታዎች መደረጋቸውን ገልጸው ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን ድጋፍ ተቀብለው  ለተፈናቃዮች በትክክል በማድረስ ፍትሃዊ የሆነ ስርጭት እንደሚያደርግ የክልሉን አደጋ መከላከል በመወከል ቃል ገብተዋል፡፡ አቶ አማረ አክለውም በቀጣይም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚጠይቀው ገንዘብ ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር በመሆኑ እና እስካሁን የተሰበሰበው ገንዘብ መጠን ብር 320000000/ሶስት መቶ ሰላሳ ሚሊዮን ብር ብቻ ስለሆነ እንደ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሁሉ ሌሎችም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ-ሰናይ ተቋማትም ድጋፍና ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያደረገውን ድጋፍም አመስግነዋል።

አቶ እያሱ መስፍን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተፈናቃዮች ምንም ባልጠበቁትና እና ባላሰቡት ሁኔታ የተፈናቀሉ በመሆናቸው በከፍተኛ እንግልትና ስቃይ ውስጥ እንዳሉ ገልፀው የህይወት መቀጠፍ አደጋ ድረስ የሆነ ችግር እንደሚያጋጥማቸውም ጠቁመዋል፡፡ ማህበረሰቡም ባለው የመደጋገፍ ባህል እንዲረዳቸው ጥሪ አቅርበው መንግስት ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት ለመመለስ እቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል።