ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከምሕረት ሜዲካል ሰፕላይስ ግሩፕ ጋር በመተባበር ለንፋስ መውጫ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

(መጋቢት 15፣2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር)፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከምሕረት ሜዲካል ሰፕላይስ ግሩፕ ጋር በመተባበር ለንፋስ መውጫ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል 14 ሚሊዬን ብር ዋጋ የሚያወጣ የሕክምና ቁሳቁስ በዛሬው እለት ድጋፍ አደረገ።

በርክክቡ ወቅት የንፋስ መውጫ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሀን ሙሉ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጦርነቱ ምክኒያት ሆስፒታሉ ውድመት ስለደረሰበት እና እሱን ተከትሎ ተቆራርጦ የነበረውን የሕክምና አገልግሎት በማስጀመር ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ተናግረዋል። ንፋስ መውጫ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታልን በመደገፍ ማጠናከር ማለት የአካባቢውን የተለያዩ ጤና ተቋማትንም ማጠናከር ማለት እንደሆነ በመጠቆም ዩኒቨርሲቲው/ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሉ ከምሕረት ሜዲካል ሰፕላይስ ግሩፕ ጋር በመተባበር ስለአደረገላቸው ድጋፍ በማመስገን ለወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳላቸው እምነታቸውን ገልፀዋል።

የንፋስ መውጫ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሙላው ጤናው በበኩላቸው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የነበረው የጠላት ወረራ እንዲመከት እና እንዲቀለበስ ዘርፈ-ብዙ አስተዋፅኦ እንዳደረገ እና ከጦርነቱ በኋላም የተከሰተውን የጉዳት መጠን በማጥናት እንዲሁም የተለያዩ ተቋርጠው የነበሩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ወደ ቀደመው ተግባራቸው እንዲመለሱ የበኩሉን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ገልፀዋል። አቶ ሙላው አክለው እሁንም ተጠናክሮ ለቀጠለው ድጋፍ በንፋስ መውጫ ሕዝብ፣በከተማ አስተዳደሩ፣ በንፋስ መውጫ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል እና በእራሳቸው ስም አመስግነዋል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን በመወከል የሆስፒታሉ ማኔጅንግ ዳይሬክተር አቶ ደመቀ ክብረኩሉ የሕክምና ቁሳቁሱን ለንፋስ ወመጫ አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ያስረከቡ ሲሆን ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ይህን እርዳታ ሲያደርግ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሆነ በመጥቀስ የዛሬው ድጋፍም በነበረው ጦርነት ምክኒያት ጉዳት ስለደረሰበት እርዳታ በማድረግ የሆስፒታሉን የሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ያለውና ተደራሽ እንዲሆን የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማበርከት እንደሆነ አብራርተዋል።

በርክክብ ፕሮግራሙ ላይ ምሕረት ሜዲካል ሰፕላይስ ግሩፕን በመወከል አቶ ቴዎድሮስ ዋለ የድርጅቱ የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ተወካይ ተገኝተዋል። አቶ ቴዎድሮስ ድርጅቱ ከውጭ ሀገር የሕክምና መድሐኒቶችንና ቁሳቁሶችን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለተለያዩ ሆስፒታሎች ድጋፍ የሚያደርግ ድርጅት እንደሆነ በመግለጽ ከአሁን በፊትም አማራ ክልል ውስጥ ላሉ 23 ሆስፒታሎች ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር እርዳታ እንደሰጠ ጠቅሰዋል።

Follow us on:
Facebook: https://www.facebook.com/cmhsbdu/
Website: http://www.bdu.edu.et/cmhs/
Telegram: https://t.me/Information-office-CMHS-BDU
Twitter: https://twitter.com/CollegeBdu?s=20

date: 
Thursday, March 24, 2022 - 14:00

Contact CMHS

College Of Medicine and Health Sciences

Bahir Dar University

 Bahir Dar, Ethiopia

Phone:- +251-0582-9 99275

P.o.box:- 79

e-mail:- collegehealthscience@gmail.com

Institutes

Website Design and Developed by LTTU,ICT Copyright © 2017- Bahir Dar University