በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር የአዲስ ዓመት መልዕክት

አዲስ ዓመት የጊዜ ዑደት አንድ ምልክት ሆኖ ያለፈን ዘመን ማክተሚያና የመጪ ጊዜን ተተኪነት ማብሰሪያ እንደመሆኑ ሁሌም በጉጉትና በተስፋ ይጠበቃል፡፡ ከአዲስ ዓመት ጋር አዲስ መንፈስ ይፈልቃል፤ ከአዲስ ዓመት ጋር አዲስ ራዕይ ይሰነቃል፤ ከአዲስ ዓመት ጋር አዲስ ዕቅድ ይወጠናል፤ ከአዲስ ዓመት ጋር አዲስ መላ ይዘየዳል፡፡
 
እንደ አገርም ሆነ እንደ ዓለም ያሳለፍነው የ2012ዓ.ም. በብዙ ውጣ ውረዶች የተሞላና “ያለፈው ዓመት” ብለን እንድንጠራው ልፍያና ትግል የጠየቀን ነበር፡፡ ዓለማችን ከየትኛውም ጊዜ በላይ በመልከ ብዙ ተግዳሮቶች የተፈተነችበት ዓመት ነበር፡፡ በተለይም የኮሮና ቫይረስ መከሰት ዓለማችን ትመራ የነበረበትን የሕይወት ዘይቤ በአያሌ አሉታዊ ሁነቶቹ በመለወጥ የሰው ልጅ ህይወት በብዙው ተገማች እንዳይሆን አድርጓል፡፡ ለሰው ልጅ ህልዉና ከጤና የበለጠ አሳሳቢ ነገር የለምና ለዚህ ዓለም-አቀፍ የጤና ችግር መፍትሔ ለማግኘት መጠነ ሰፊ ትግል እየተደረገ ይገኛል፡፡
 
የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ኢትዮጵያ ከተከሰተበት ወቅት አንስቶም በየአቅጣጫው እየተፈተንን እንገኛለን፡፡ የወረርሽኙ ተፅዕኖ በግለሰቦች አኗኗር፣ በአገር ኢኮኖሚ፣ በወጣቶች ትምህርትና መለወጥ፣ በሕጻናት ደስታና ተስፋ እንዲሁም በእያንዳንዳችን የዕለት ከዕለት ውሎ ላይ ብርቱ ክንዱን አሳርፏል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ዓለም በአዲስ የአኗኗር መንገድ መራመዷ ግድ ሆኗል፡፡ ጠንካራ መሰረት በለሌዉ የአገራችን የጤና ስርዓት የሕክምና ተቋማት የችግሩ ዋና ገፈት ቀማሽ በመሆናቸው በዉሱን ሀብት መደበኛ የሕክምና አገልግሎትን ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚደረገው ሁሉን አቀፍ ስራ ጋር አቻችሎና አጣጥሞ ለማስሄድ ብርቱና ፈታኝ ጥረት አድርገዋል፤ በማድረግም ላይ ናቸው::
 
ይሁን እንጂ ከተከሰቱት ጎታች ሁነቶች ይልቅ ያሳካናቸው ተስፋ-ሰጪ ውጤቶች ያመዝናሉ፡፡ ላጋጠሙን መሰናክሎች የተሰጡት አብዛኖቹ ምላሾች አበረታች እንደመሆናቸው ከመልካም ውጤቶች ለመማርና የተሰሩ ስህተቶችን ለማረም አዲሱ ዓመት ሌላ የተነሳሽነት መንፈስ ይዞልን መጥቷል፡፡ እንደግለሰብም ሆነ እንደተቋም ባሉን መልካም እሴቶች ላይ በመገንባት ወደፊት መጓዝ አገርን ለማሳደግም ሆነ ሕብረተሰባችንን ለማገዝ ብቸኛው አማራጭ ነው፡፡ ከዜሮ መጀመርን በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ እንደአዙሪት በነበርንበት ቦታ ላይ መልሶ ከማስቀመጥ ውጪ የፈየደልን አንዳችም ነገር የለም፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ እየሰራ በሚገኝባቸው አራት ዘርፎች ማለትም መማርና ማስተማር፣ ጥናትና ምርምር፣ ማሕበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት እና ሕክምና ጉልሕ አስተዋፅኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ለዚህም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችንና ሰራተኞችን፣ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በስሩ የሚገኘው የጥበበ ጊዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አባላት፣ በአገርም ውስጥ ሆነ ከአገር ውጪ ሆነው ኮሌጁንና ሆስፒታሉን በማገዝ ላይ የሚገኙ ወዳጆቻችንን እንዲሁም ኮሌጃችን በሚገኝበት አካባቢ የሚኖረውን ማሕበረሰብ እጅግ አድርጌ ላመሰግን እወዳለሁ፡፡
 
በኮሌጃችን እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ምክንያት ከፊታችን ብሩህ ጊዜ ይጠብቀናል፡፡ የምናገኛቸውንም መልካም አጋጣሚዎች በሙሉ ተጠቅመን የሚገጥሙንን ፈተናዎች በብልሃትና በጥበብ እየተወጣን ኮሌጃችንንና ዩኒቨርሲቲያችንን በማሳደግ አገልግሎቶችን በተሻለ ጥራትና ብቃት ለመስጠት ከምንጊዜውም በላይ ተቀራርበን፣ ተረዳድተንና ተራርመን መስራት ይጠበቅብናል፡፡
አዲሱ የ2013ዓ.ም. ዕቅዶቻችንን የምናሳካበት፣ ለችግሮቻችን መፍትሔ የምናገኝበትና ተደጋግፈንና ተከባብረን በበጎ የምንለወጥበት እንዲሆንልን እመኛለሁ፡፡
 
አገራችንንና ህዝቦቿን አብዝቶ ሰላም ያድርግልን!
 
በዓሉን ስናከብር እራሳችንን፣ ቤተሰባችንንና ወገኖቻችንን ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ተገቢዉን ጥንቃቄ እናድርግ!
 
መልካም አዲስ ዓመት!
 
ፕ/ር የሺጌታ ገላው (በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር)

Contact CMHS

College Of Medicine and Health Sciences

Bahir Dar University

 Bahir Dar, Ethiopia

Phone:- +251-0582-9 99275

P.o.box:- 79

e-mail:- collegehealthscience@gmail.com

Institutes

Website Design and Developed by LTTU,ICT Copyright © 2017- Bahir Dar University