አገር-በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ህክምና ጋር በማቀናጀት የአዕምሮ ሕክምናን ማሳደግ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና በአንዳሳ ደብረ መንክራት ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መካከል የአዕምሮ ሕክምናን በተቀናጀ መልኩ ለማሳደግ “አገር-በቀል ዕውቀትን ከዘመናዊ ሕክምና ጋር በማጣመር የአዕምሮ ጤና እንክብካቤን ማሳደግ” በሚል መሪ ቃል ነሐሴ 15፣2012 ዓ.ም በሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጥበበ ግዮን ግቢ በስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል አዘጋጅነት ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ዓላማ

የውይይቱ ዓላማ በአገራችን በተለይም በክልላችን በአዕምሮ ህመም ምክንያት የሚደረሰውን መጠነ-ብዙ ተጽዕኖ መቀነስና የአዕምሮ ህመም ታማሚዎችን የተቀናጀ የመንፈሳዊ ወይም የፀበልና የዘመናዊ ሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የታማሚዎችን የአዕምሮ ጤና በማሻሻል፣ ቤተሰቦቻቸውና አገር ላይ የሚደረሰውን ጫና በመቀንስ ለህብረተሰባቸው ብሎም ለአገራቸው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማገዝ ነው። ከሌጁ ከተሰማራባቸው አራት አብይ ዓላማዎች ማለትም መማር-ማስተማር፣ ማህበረሰብ አገልግሎ፣ ምርምር እና ሕክምና ስራ አንፃር የሚኖረው ቀጥተኛ ጥቅም ከፍተኛ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ አገር በቀል ጥበብንና ዕውቀትን በዘመናዊ መንገድ በምርምር በማገዝ ዩኒቨርስቲው ላስቀመጠው በቅርቡ በአፍሪካ ከምርጥ የምርምር ተቋማት አንዱ የመሆን ዕራይ ለማሳካት የሚኖረው ጠቀሜታው የጎላ ነው። 

የውይይቱ ተሳታፊዎች

በውይይቱም የሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት የተጋበዙ ሲሆን በዋናነት ግን የአንዳሳ ደብረ መንክራት ገዳም አስተዳዳሪና ካህናት አባቶች፣ አጥማቂያን፣ ሰባኪያን፣ የአንዳሳና አካባቢው ታዋቂ ሰዎችና የሃገር ሽማግሌዎች፣ ከአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ፣ ገዳሙ የሚገኝበት ወረዳ ማለትም ከባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት፣ የአንዳሳ ጤና ጣቢያ ሃላፊና ከበባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕረዘዳንት ቢሮ ማለትም የአስተዳደርና ቢዝነስ ም/ፕረዘዳንትና ከሕ/ጤ/ሳ/ኮ ዋና ስራ አስፈጻሚ እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የውይይቱ ይዘት

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ አስተዳደርና ቢዝነስ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ መድረኩን  በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ካስከፈቱ በኋላ የኮሌጁ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው የውይይቱን ዓላማ በማስተዋወቅ ውይይቱን አስጀምረዋል፡፡ በስነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል በኩል ስለ አዕምሮ ጤና እና አዕምሮ ህመም ለተውያዮች የመነሻ ፅሁፍ የቀረበ ሲሆን ለሚታቀዱ ስራዎች ክንውን ሲባል በተቀናጀ መልኩ የአዕምሮ ታማሚዎችን በመንከባከብ ከሚሰሩት ተቋማት ማለትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ከዕንጦጦ ኪዳነ-ምህረትና ከሽንቁሩ ሚካኤል ገዳማት ጋር እየሰሩበት ያለው ተሞክሮ (ልምድ ልውውጥ) ለታዳሚዎች ቀርቧል።  

ከዚህ በመቀጠል መድረኩ ‘እኛስ እንዴት በቅንጅት መስራት እንችላልን?’ በሚል የውይይት መነሻነት፣ እንግዶች ሃሳብ እንዲያናሸራሽሩ ተደርጓል፡፡ ከአንዳሳ ደብረ-መንክራት የመጡ አባቶች ገዳሙ ከዩኒቨርስቲው ጋር የነበረው ግንኙነት የቆየ እንደሆነና በተለይም የተለያየ ወረርሽኖች ሲከስቱ (ለምሳሌ ወባ፣ አተት) ኮሌጁ የጤና ባለሙያዎችን በመላክ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ከገለፁ በኋላ አሁንም የአዕምሮ ህምም ያለባቸው ምዕመናን በገዳሙ በጣም በከፍተኛ ቁጥር ስለሚገኙና ከፀበል ውጭ ዘመናዊ ሕክምና ስለማይከታተሉ የቅንጅት ስራውን መጀመር አድንቀው ከዩኒቨርስቲው ጋር አብረው መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ከተወያዮች ተነስተዋል፡-

  1. በቅንጅት ከገዳሙ ጋር ሊሰሩ የታቀዱ ስራዎች በግልጽ መቀመጥ አንደሚኖርባቸውና ጥናት ላይ የተደገፉ እንዲሆኑ ቢደረግ፣
  2. ከገዳሙ ጋር ሊሰሩ የታሰቡ ስራዎች በፍጹም የቤተክርስቲያኗን ዶግማ የማይነኩና የአካባቢውን ማሕበረሰብ ወግና ባህል ያከበረ መሆን እንደሚገባው፣
  3. ከገዳም አባቶችና ከዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ ኮሜቴ ተዋቅሮ የሚሰሩ ስራዎች ክትትል ቢደረግባቸው ቶሎ ለማረምና ለማስተካከል እንደሚያግዝ፣
  4.  ዩኒቨርስቲው ወይንም ኮሌጁ ለገዳሙ የሚያስፈልጉ ስልጠናዎችን ቢሰጥና አቅጣጫ ቢያስይዝ፤
  5.  የምዕመናን የአዕምሮ መድኃኒት መከታተልም (ዘመናዊ ሕክምና መከታተል) ከገዳሟ አሰራር ውጭ እንዳልሆነና ለዚህም ገዳሟ በቀጥታ እንደምታግዝ፤
  6. ወደ ገዳሙ የሚመጡ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኝ መሆን አንደሚገባቸውና ከዩኒቨርስቲው በደብዳቤ ህጋዊነታቸውን በማረጋገጥ አንዲላኩ፣ ወደ ገዳሙ ለዚህ ስራ ተብሎ ከመጡ በኋላ የሚሰሩት ስራም በስምምነታችን ላይ የተፈቀዱትን ብቻ መሆን እንደሚኖርበት ገልጸዋል።

በውይይቱ ላይ የታደሙ የአካባቢው ታዋቂ ሰዎችና ሽማግሌዎችም በበኩላቸው የቅንጅት ስራው ለአዕምሮ ታማሚዎች የሚሰጥው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንና ለአካባቢ ማህበረሰብም መልካም እድል መሆኑን ገልጸው የሚከተሉትን አንኳር ነጥቦች አንስተዋል፡፡

  1. የአካባቢው ማሕበረሰብ የገዳሙ ጠባቂ እንደመሆኑ መጠን ገዳሙ ጋር የሚሰሩ የቅንጅት ስራዎች ለማሕበረሰቡ በተለያየ መንገድ በማስተዋወቅ ጠቀሜታውን ማስተማር አንደሚገባ ፣
  2. ምንም እንኳን ሕበረተሰቡ አማኝ እንደሆነና ለማንኛውም የአዕምሮ ህመም ጸበል ቦታ እንደሚያዘወትር ቢታውቅም በእርኩስ መንፈስ የሚመጣውን የኦዕምሮ ህመም በፀበል መከላከልና ማዳን ቢቻልም በተለያዩ ችግሮች ለሚከሰትን ጭንቀት ግን ዘመናዊ ህክምና እንደሚያስፈልግ ለማህበረሰቡ ትምህርት ቢሰጥ መልካም እንደሆነ፤ለምሳሌ፣ አንድ ገበሬ ቀንጃው በሬ (ብቸኛ በሬው) ቢሞትበትና በአዕምሮ ጭንቀት ቢታመም ይህ በምክር አገልግሎትና በዘመናዊ ህክምና ሊድን ይችላል እንጂ በፀበል ስለማይደን የተቀናጀ የአዕምሮ ጤና እንክብካቤ ለዚህ ዓይነቱ የአዕምሮ ጭንቀት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
  3.  ምንም እንኳን አንዳንድ የአካባቢው የአዕምሮ ታማሚዎች አልፎ አልፎ ወደዘመናዊ ሕክምና ሂደው መድኃኒት ቢሰጣቸውም በቤተሰቦቻቸው ጫና ወደ ፀበል ቦት ሲወሰዱ አንዳንድ የእምነት አባቶች መድኃኒት መውሰድ እምነትን ማጓደል እንደሆነ በመገሰጽ መዳኃኒታቸው እንዲቋረጥ ምክንያት ስለሚሆኑ የቅንጅት ስራው ይህን መሰል ችግር ያስቀርልናን መልካም ነው ሲሉ የአካባቢው ሽማግሌዎች ጠቀሜታውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአንዳሳ ጤና ጣቢያ ኃላፊም የቅንጅት ስራው በጣም አስፈላጊና ለማህበረሰቡ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸው ጤና ጣቢያውም የሚጠበቅበትን ለማገዝ ፍቃደኛ መሆኑንና ከገዳሙና ዩኒቨርስቲው ጎን ሆኖ ህብረተሰቡን ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አስረድተው ስራው ውጤታማ እንዲሆን ከሦስቱ አካላት ማለትም ከዩኒቨርስቲው፣ ከገዳሙ አባቶች እና ከአንዳሳ ጤና ጣቢያ ኮሚቴ ተዋቅሮ ቢሰራ መልካም እንደሆነ ገልጸዋል።

የዩኒቨርስቲው የአስተዳደርና ቢዝነስ ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የገዳሙ አባቶች የዩኒቨርስቲውን ጥሪ አክብረው ለውይይት ስለመጡ አመስግነው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ምክንያት አለመገኘታቸውን ጠቅሰው ዩኒቨርስቲውን በመወከል ከገዳሙ ተወያዮችና ከአገር ሽማግሌዎች ለተነሱት ሐሳቦች ማብራሪያ በመስጠት ለቅንጅት ስራው ውጤታማነት የሚያግዙ መሰረታዊ ስራዎችን አንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ አክለውም የሚከተሉትን ነጥቦችና የውሳኔ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፤

  1. የቅንጅት ስራው በሚሰራበት ወቅት ሊፈጠር የሚችልን ስጋት ለመከላከል በገዳሙ አባቶች በኩል የገዳሟን ዶግማ ከማስጠበቅ አንፃር ለተነሱት የጥንቃቄ ሐሳቦች፣ ዩኒቨርስቲው በኮሌጁ በኩል የዕቅድ ትውውቅ ፕሮግራም እንደሚያዘጋጅና የሚሰሩ ስራዎች በግልጽ ለውይይት እንደሚቀርቡ፤
  2. ዘላቂነቱን ለማስጠበቅና ለገዳሙ ስራ አመችነት ሲባል ዩኒቨርስቲው ከገዳሙ ጋር የጋራ ስምምነት እንደሚያዘጋጅና በቅርቡ እንዲያስፈጽም፤
  3. የሚያስፈልጉ የሙያ ስልጠናዎች ለገዳሙ አባቶችና አባላት በኮሌጁ በኩል እንደሚዘጋጅና እንደሚሰጥ ገለጸዋል።

የሕክምናና ጠየና ሳይንስ ኮሌጁ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር የሺጌታ ገላው በበኩላቸው ኮሌጁ ገዳሙ ድረስ ሄዶ መወያየት ሲገባው ካለው የመሰብሰቢያ ቦታ አመችነት አንፃር አባቶችን ወደ ኮሌጁ እንዲመጡ መደረጉ የማንገላታት ባህሪ ቢኖረውም አባቶች ግን በተያዘው ቀጠሮ መሠረት በመገኘታቸው ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ፕሮፌሰር የሺጌታ የእምነት አባቶች ለሕክምና ሙያና አገልግሎት እጅግ እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው ካሁን በፊትም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስትሰራበት እንደቆየች ጠቅሰው ይህ የቅንጅት ስራ የዘገየና የኮሌጁ ድክመት መሆኑን ገልጸው አሁንም ጥሩና መልካም አጋጣሚ እንደሆነና ኮሌጁ በስነ-አዕምሮ ህክምና ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ሙያዎች ከገዳሙ ጋር በጋር መስራቱ የሚኖረውን የላቀ ጠቀሜታ አብራርተዋል። ፕሮፌሰር የሺጌታ ከዚህም ጋር አያይዘው የእምነት አባቶች በየእምነታቸው ሆስፒታል ድረስ እየመጡ ታማሚዎችን እንዲጠይቁና ለታማሚዎች የመንፈስ ጥንካሬ እንዲሰጡ ለወደፊቱ ይመቻቻልም ብለዋል።

ቀጣይ ስራዎች

በመጨረሻም ከገዳም አባቶችን፣ ከዩኒቨርስቲውን ማሕበረሰብና ከአካባቢው ሽማግሌዎች የተውጣጣ ኮሜቴ ተዋቅሮ ቀጣይ የቅንጅት ስራዎች እንዲሰሩ በመወሰን ውይይቱ በጥሩ ሁኔታ ተቋጭቷል።

Contact CMHS

College Of Medicine and Health Sciences

Bahir Dar University

 Bahir Dar, Ethiopia

Phone:- +251-0582-9 99275

P.o.box:- 79

e-mail:- collegehealthscience@gmail.com

Institutes

Website Design and Developed by LTTU,ICT Copyright © 2017- Bahir Dar University