የሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ ሉኡካን ቡድን ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ጋር አብሮ የመስራቱን ስምምነት ወደ ትግበራ እንደሚለውጥ ይፋ አደረገ

በኢንዶኖዢያ ውስጥ የሚገኘው የሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ም/ፕሬዚዳንት የሚመራው ቡድን ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ ጋር የተፈራረመውን ስምምነት ወደ ትግበራ ለመቀየር ውይይት አካሄደ

የባህርዳር ዩኒቨርስቲ በርካታ ስምምነቶች ወይም ፖርትነርሽፖች ቢኖሩትም ከመፈራረም የዘለለ መሬት የነካ ሥራ ሲያካሂድ እምብዛም ባይታይም ከኢንዶኖዧያ የመጣው የሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ ሉኡክ ግን ለወደፊት ከዩኒቨርስቲያችን ጋር በባዩቴክኖሎጂና በሌሎች የሥራ መስኮች ወደ ትግበራ በመግባት በርካታ አኩሪ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልፆል፡፡

ቡድኑ ያካተታቸው የኢንዶኖዧያ አምባሳደር በኢትዮጵያ እጅግ የተከበሩ አምባሳደር ኢማም ሳንቶሶ፣ በኢንዶኖዧያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የአፍሪካ ጉዳዩች ዳሬክቶሬት ም/ዳይሬክተር አቶ ፌሪ ኢሷዋንዲ፣ የሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ ም/ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሱታርኖ እና ሌሎችንም ያካተተ ሲሆን በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ባይሌ ዳምጤ የመግቢያ ንግግር ሲያደርጉ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነና ጥራት ያለው ምርምር ለማካሄድ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስገንዝበው ለውይይቱ የመጣውን ሉኡክ ካመሰገኑ በኋላ ማንኛውንም ነገር እጅ ለእጅ በመያያዝ በተለይ በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተጠናከረ ሥራ በመሥራት የሁለቱን ዩኒቨርስቲዎች ግንኙት ማዳበር እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

አምባሳደሩም በበኩላቸው በሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ ሥር ያሉ ፕሮግራሞችንና የተለያዩ ሥራዎችን አስተዋውቀው ለወደፊቱ ቴክኖሎጂን ከማላመድ ጋር የተያያዙ በርካታ ሥራዎችን በመስራት የሁለቱን ዩኒቨርስቲዎች ጥምረት ማጠናከር እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

አምባሳደሩ አያይዘው በተጨባጪ አሁን ሊሰሩ የታሰቡት ዋና ዋና ተግባራት የሩዝና የወተት ምርት ማሳደግ፣ የዶክትሬት ድግሪ ተማሪዎችን ማማከር፣ የጋራ ፕሮጀክት መቅረፅ በተለይም በእንስሳት ስነ-ዘር እና ዝርያ ማሻሻያ ላይ የተለየ ትኩረት በመስጠት አብሮ መስራት፣ እና በዓሣ ሀብት ልማት ዙሪያ ጣና ሀይቅን በመጠቀም በርካታ የሥራ ዘርፎችን ማከናወን እንደሚቻል ገልፀው ሁለቱ ዩኒቨርስቲዎች በተለያዩ የአካዳሚክ ክፍሎች ላይ የጋራ ውይይት በማካሄድ አብሮ መሥራት እንደሚቻል አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ በፕሮፌሰር ሱታርኖ እና ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ የባዮቴከኖሎጂ ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ከፍያለው አለማየሁ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ታዳሚው ሰፊ ውይይት አካሂዶ ለተነሱት ጥያቄዎች ጽሁፍ አቅራቢዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ጥምረቱን ከመቸውም ጊዜ በላይ ማጠናከር እንደሚቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ተከናውኗል፡፡

በምክክር መድረኩ ወቅት ከተዘረዘሩት ተግባራት በተጨማሪ ከአሁን በፊት ስምምነቱ ሲፈረም የባህርዳር ዩኒቨርስቲ የበላይ አመራር አካላት ኢንዶኖዢያ ውስጥ ከሚገኘው ሴበላስ ማርት ዩኒቨርስቲ ሂዶ ስምምነቱን በተፊራረመው መሠረት በአምስት ዓመት ውስጥ የሚሰሩት ሥራዎች መርሀ ግብር (Action Planne) በመንደፍ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡   

ከውይይቱ ባሻገር በባህርዳር ዩኒቨርስቲ ግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ሥር የሚገኙትን የከብት እርባታ ቦታ፣ የበግ እርባታ እና የተለያዩ ቤተ-ሙከራዎችን ሉኡኩ ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡

ካሉት ቤተ-ሙከራዎች መካከል የባዮቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራው ዘመናዊ የሆነ መርጃ መሳሪያዎች መሟላታቸውን ማየት ተችሏል፡፡