Jump to navigation
የዳይሬክተሩ መልእክት ዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማእከል በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ሥር ከሚገኙ ዘጠኝ የምርምር ማእከላት መካከል አንዱና ገና በማደግ ላይ ያለ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀለል ባለ አነጋገር የምርምር ማእከላት ራእይና ተልእኮ በበሀገር አቀፍ፣ አህጉር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ጥሩ ከሚባሉ የምርምር ማእከላት የእድገት ደረጃ ላይ ደርሶና ተወዳዳሪ ሆኖ የሚፈለገውን ውጤት በማምጣት ምርትንና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ አንድ የባህል ማእከል ደግሞ ማኅበረሰቡ ለዘመናት በማኅበራዊ ሕይወቱ ሲጠቀምበት የነበረውን ሀገር በቀል ዕውቀቱን አጥንቶ፣ መርምሮ፣ መዝኖና ሰንዶ የተሻለውን ባህል ማሳደግ፣ ጎታች የሆነውን ደግሞ በተሻለው በመለወጥና በብዙ መልኩ ጠንካራ የሆነ የሥራ ተነሣሺነትን በመጨመር ለተሻለ የእድገት ደረጃ ከፍተኛ አስተወጽኦ ማድረግ ነው፡፡ ሀገር በቀል እውቀት ዛሬ ላይ ሆነን ሀገራችን ወደፊት ትደርስበታለች ለምንለው ራእይ መቼም ቢሆን የማያጠራጥር ጠንካራ መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ በተለይ ሀገር በቀል ምሁራን ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ ሰፊ ታሪክና ባህል ካላቸው ጥቂት ሀገሮች መካከል አንዷ እንደ መሆኗ መጠን ያልጠናና ተዝቆ የማያልቅ ሀገር በቀል ዕውቀት ያላት መሆኗን በመገንዘብ የጥናትና ምርምር እንቅስቃሴያችሁን በሀገር በቀል ዕውቀት ላይም እንድታደርጉ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ የምርምር ማእከላችን በዚህ መስክ ጥናትና ምርምራቸውን የሚያካሂዱ ምሁራንን ያበረታታል፡፡ ሙሉቀን አንዱዓለም (ዶ/ር) የዐባይ ባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማእከል ዳይሬክተር