#የዓይን_መንሸዋረር

#የዓይን_መንሸዋረር

===============

በተፈጥሮ ሁለት ዓይኖች እያሉን ለምን አንድ ነገር ለማየት ስንሞክር ሁለት ሆኖ እንደማይታየን እራስዎን ጠይቀዉ ያዉቃሉ!?

በሁለት ዓይኖቻችን አንድ ነገር ስናይ ሁለት ሆኖ የሚታይ ከሆነ በእይታችን ላይ ችግር ይፈጠራል። ስለሆነም ይህ እንዳይሆንና ሰብአዊ ፍጡር እንዳይቸገር ሁለቱ ዓይኖች በቅንጅትና በጥምረት በመሥራት አንድ ምስል ብቻ እንድናይ በሚያስችል መንገድ ተፈጥረዋል። በኅብረትም ሥራቸዉን ይከዉናሉ። አንጎልም ከሁለት ዓይኖች የደረሰዉን መረጃ በይበልጥ በማቀናጀትና ወጥ ትርጉም በመስጠት አንድ የጥምረት እይታ ብቻ እንዲኖር ያደርጋል።

ችግር የሌለበት አንድ የጥምረት እይታ እንዲኖር ለማድረግ ደግሞ፡-

1. ጤንነቱ የተጠበቀ ዓይንና የዕይታ መስመር፤

2. የዓይን ሚዛናዊ እንቅስቃሴና ቁጥጥር፤ እንዲሁም

3. ጤንነቱ የተጠበቀ የዕይታ አንጎል ሊኖር ይገባል።

ከሦስቱ አስፈላጊ ነገሮች በአንዱ ወይም በሁለቱ ላይ ችግር ከተፈጠረ አንድ የጥምረት እይታ የመኖሩን ነገር አዳጋች ብሎም የማይቻል ሊያደርገዉ ይችላል። ሁለቱ ዓይኖችም ወደ አንድ አቅጣጫ በጋራ ለማየትና ተልእኳቸዉን ለመወጣት ይቸገራሉ።

ይህ የተፈጥሮ የእይታ ሚዛን ከተዛባ የምናየዉ ነገር ጥልቀትና ይዘት ይዛባል። ችግር ያለበት ዓይንም መደበኛ ማዕከላዊ ቦታዉን ለቆ ወደ ዉጭ (ወደ ጆሮ አቅጣጫ) ወይም ወደ ውስጥ (ወደ አፍንጫ አቅጣጫ) እንዲሁም ወደ ላይ (ወደ ግንባር አቅጣጫ) ወይም ወደ ታች (ወደ ጉንጭ አቅጣጫ) ያዘንብላል። በዚህም ምክንያት አንድ ነገር ላይ አተኩረን በምናይበት ጊዜ ሁለቱ ዓይኖች ወደ ተለያየ አቅጣጫ ይመለከታሉ። በተጨማሪም አንድ ነገር ስናይ ሁለት ሆኖ ሊታየን የሚችልበት ሁኔታ ይፈጠራል።

#የዓይን_መንሸዋረር_ምንድን_ነዉ?

ሁለቱ ዓይኖች ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሲመለከቱና አንዱ ወይም ሁለቱ ዓይኖች መደበኛ ማእከላዊ ቦታዉን ለቆ ወደ ዉጭ ወይም ወደ ውስጥ አለያም ወደ ላይ ወይም ወደ ታች ሲያዘነብል የዓይን መንሸዋረር (በእንግሊዝኛዉ አጠራር ‹‹ስትራቢዝመስ››) ተብሎ ይጠራል (ምሥል 9.1 ይመልከቱ)።

 

#የዓይን_መንሸዋረር_ለምን_ይከሰታል?

ይህ የመንሸዋረር ችግር በብዛት የሚከሰተዉ በዓይን ጡንቻዎች የኃይል ሚዛን መዛባት ምክንያት ሲሆን በአጠቃላይ በዉበት ላይ ከሚያመጣዉ ተጽእኖ ባሻገር እይታ እንዲቀንስ ብሎም የህጻናትና የልጆች ዓይን እንዲሰንፍ ሊያደርግ ይችላል። እያንዳንዱ ዓይን ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሚዛናዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የሚያስችሉ 6 ጡንቻዎች (ምሥል 9.2 ይመልከቱ) ያሉት ሲሆን የሁለቱ ዓይን ጡንቻዎች ሁለቱ ዓይኖች ቅንጅታዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸዉ ለማስቻል በኅብረት ይሠራሉ።

በአጠቃላይ የሁለቱን ዓይኖች እንቅስቃሴ የሚቆጣጠሩ ዐሥራ ሁለት (12) ጡንቻዎች ሲኖሩ እነዚህ የዓይን ጡንቻዎች በሰዉነታችን ዉስጥ ከሚገኙ ጡንቻዎች ሁሉ የበለጠ ንቁና ፈጣን እንቅስቃሴ በማድረግ ይታወቃሉ።

የእነዚህ ፈጣን ጡንቻዎች የእንቅስቃሴ ኃይል ሚዛን በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች ሊዛባ ይችላል። እነሱም፡-

1. ሚዛኑን ያልጠበቀ የጡንቻ ኃይል (የበዛ ወይም ያነሰ)

2. ግድፈት ያለበት የነርቭ ሞገድ ለጡንቻ መድረስ (የበዛ ወይም ያነሰ) እና

3. ግድፈት ያለበት አነጣጥሮ የማየት ችግር ናቸዉ።

ሚዛኑን ያልጠበቀ የጡንቻ ኃይልና ግድፈት ያለበት የነርቭ ሞገድ በተለያዩ የጤና ችግሮች ሊከሰት የሚችል ሲሆን በብዛት ግን የሚታወቅ ዋና መንስኤ ሳይኖረዉ ይከሰታል። የተወሰኑ ጨቅላ ህጻናት ሲወለዱ የዓይን መንሸዋረር ችግር ሊኖርባቸዉ ይችላል። በተወሰኑት ላይ ደግሞ ከተወለዱ በኋላ ይከሰታል። በጥቅሉ ይህን መሰል ችግር ከሚያስከትሉ የታወቁና ተጠቃሽ መንስኤዎች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸዉ፡-

1. በጡንቻዎች ላይ የሚደርስ ቀጥተኛ ጉዳት፤

2. ጡንቻዎችን በሚያንቀሳቅሱ ነርቮች ላይ የሚደርስ ጉዳት /ችግር/፤

3. ጡንቻዎችን በሚመግቡ የደም ሥሮች ላይ የሚደርስ ጉዳት /ችግር/፤

4. በተፈጥሮና በሌሎች ምክንያቶች የሚደርስ የኃይል መዛባት ችግር፤

5. በሌሎች የዓይን ጤና ችግሮች (ለምሳሌ፡- በመነፅር ሊስተካከል የሚችል የእይታ ችግር፣ የዓይን ካንሰር፣ ወዘተ)።

 

ኩፍኝ፣ የስኳር ህመም፣ መርዛማ የእንቅርት ችግር፣ የጭንቅላት እጢ፣ የጭንቅላት ደም መፍሰስ፣ በጭንቅላት ላይ የሚደርስ የምት አደጋ እንዲሁም አንዳንድ የዓይን ቀዶ ሕክምናዎች በጡንቻዎች በነርቮች ወይም የደም ሥሮች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ስለሚችሉ ለዓይን መንሸዋረር ችግር መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ።

ሚዛኑን ያልጠበቀ የጡንቻ ኃይል ወይም የነርቭ ሞገድ ግድፈት ያለበት ዓይን ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሊንሸዋረር ይችላል። ለምሳሌ፡- የዉሥጠኛዉ የጡንቻ ኃይል ከዉጨኛዉ ከበዛ ችግሩ ያለበት ዓይናችን ወደ ዉሥጥ (ወደ አፍንጫ አቅጣጫ) የሚንሸዋረር ሲሆን የዉጨኛዉ የጡንቻ ኃይል ከዉሥጠኛዉ ከበለጠ ደግሞ ዓይናችን ወደ ዉጭ (ወደ ጆሮ አቅጣጫ) ይንሸዋረራል (ምሥል 9.3 ይመልከቱ)።

በተመሳሳይ መንገድም በዓይን የዉሥጥና የዉጭ ጡንቻዎች መካከል ያለዉ የመሳብ ኃይል ካልተመጣጠነ ዓይን ኃይል ወደ በዛበት ጡንቻ አቅጣጫ ስለሚጎተት (ስለሚሳብ) የዓይናችን መእከላዊ ክፍል (ብሌን) መደበኛ ቦታዉን ለመልቀቅ ይገደዳል። ይህ ጊዜያዊ ወይም ቋሚ የተቃራኒ ዓይነ ጡንቻዎች የመሳብ (የመጎተት) ኃይል መለያየት መንሸዋረር እንዲከሰት ያደርጋል።

 

#የዓይን_መንሸዋረርን_ክምና_ማስተካከል_ይቻላልን?

የዓይን መንሸዋረር ከሚያስከትለዉ የእይታ ችግር ባሻገር በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት፣ በስነልቦና፣ በራስ መተማመን እንዲሁም የሥራ እድል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ስለሚያስከትል በሕክምና መስተካከል ይኖርበታል። ተገቢዉን ሕክምና በማድረግም ዓይን መደበኛ ቦታዉን እንዲይዝና ሁለቱም ዓይኖች ወደ አንድ አቅጣጫ በጋራ ማየት እንዲችሉ ማድረግ ይቻላል። የሚደረገዉ ሕክምና እንደ ችግሩ መንስኤና ደረጃ የሚለያይ ቢሆንም ዋና ዋና የሕክምና ዓይነቶች የሚከተሉት ናቸዉ (በዝርዝር ለማወቅ ከፈለጉ የዓይን ጤናና እንካብካቤ መጽሐፍን ከገጽ 118-120 ያንብቡ)።

ሀ. የመነጽር ሕክምና፡

በእይታ ችግር ምክንያት የመጣ በህጻናትና ልጆች ላይ የሚከሰት የመንሸዋረር ችግር ተገቢዉን መነጽር በማድረግ ሊስተካከል ይችላል። ስለሆነም ይህ ዓይነት ችግር ያለባቸዉ ልጆች ተገቢዉን የእይታ መነጽር ሁልጊዜ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

ለ. የዓይን አካል ብቃት እንቅስቃሴ፡

ለተወሰኑ አይነት በተለይም ከድካም ስሜትና የቅርብ እይታ ከሚጠይቅ ሥራ (ንባብ፣ ጥልፍ፣ ስፌት፣ የኮምፒዩተር ሥራ፣ ወዘተ) ጋር ተያይዘዉ ለሚመጡ የመንሸዋረር ችግሮች የዓይን ጡንቻን ብቃት የሚጨምር እንቅስቃሴ ማድረግ ሊጠቅም ይችላል።

ሐ. የዓይን መንሸዋረር ቀዶ ህክምና፡

ይህ ዋናዉ የጡንቻ ኃይል የማመጣጠኛ የሕክምና ዘዴ ሲሆን ሌሎች አማራጮች ዉጤታማ መፍትሄ በማይሆኑበት ጊዜ ይደረጋል። የጡንቻ ኃይል የማመጣጠን ቀዶ ሕክምናዉ በዋናነት ጉልበት ከበዛበት ጡንቻ ጉልበት በመቀነስ እንዲሁም የመሳብ ኃይሉ ደካማ ለሆነዉ ጡንቻ ጉልበት በመጨመር ሚዛናዊ ተቃራኒ የጡንቻ ጉልበት እንዲኖር በማድረግ የዓይናችንን አቀማመጥ ማስተካከል ነዉ። የዓይን መንሸዋረር ቀዶ ሕክምና በዚሁ ጉልበት የማመጣጠን ሳይንሳዊ ቀመር የሚከናወን ነዉ (ምሥል 9.9 ይመልከቱ)። በብዛት ቀዶ ህክምናዉ የሚደረገዉ የዓይን መንሸዋረሩ ባለበት ዓይን ላይ ሲሆን የኃይል አለመመጣጠኑ በጣም ከፍተኛ ከሆነ የሚደረገዉን ቀዶ ሕክምና የበለጠ ዉጤታማ ለማድረግ ቀዶ ሕክምናዉ በሁለቱም ዓይኖች ላይ ሊደረግ ይችላል።

 

#የዓይን_መንሸዋረር_ሲኖር_ሐኪም_ማማከር_ያለብን_መቼ_ነዉ?

እድሜአቸዉ ከሦስት ወር በታች የሆኑ ህጻናት በተለይም ጨቅላ ህጻናት ምንም ዓይነት የጤና ችግር ሳይኖር አልፎ አልፎ ዓይናቸዉን ሊያጠናግሩ ይችላሉ። በተለይ ደግሞ ህጻናት የድካም ስሜት ሲሰማቸዉ ይህን ያደርጋሉ። ይህ የተለመደና ያለምንም የጤና ችግር የሚመጣ በመሆኑ ብዙ አሳሳቢ አይደለም። ይሁን እንጂ ለሚከተሉት የመንሸዋረር ችግሮች የዓይን ሐኪም ማማከር የግድ ያስፈልጋል (በዝርዝር ለማወቅ ከፈለጉ የዓይን ጤናና እንካብካቤ መጽሐፍን ከገጽ 120-121 ያንብቡ)።

1. ከሦስት ወር እድሜ በላይ ያላቸዉ ህጻናት ዓይናቸዉን የሚያጠናግሩ ከሆነ፤

2. መደበኛ ያልሆነ የጭንቅላት አቀማመጥ ካላቸዉ እና

3. ከዓይን መንሸዋረር ችግር ባሻገር ሌሎች ምልክቶች ከታዩ::

በአጠቃላይ የዓይን መንሸዋረር ችግር ከሚያመጣዉ ቀጥተኛ የዉበትና ተያያዥ የስነልቦና ችግር፣ የእይታ መቀነስና የዓይን መስነፍ ችግር ባሻገር የዓይን መንሸዋረር ከባድና ሕይወት አስጊ ለሆኑ የዓይንና ሌሎች የጤና ችግሮች (ለምሳሌ የዓይን ካንሰር፣ የጭንቅላት እጢ የጭንቅላት ዉስጥ ደም መፍሰስ፣ ወዘተ) መከሰት አመልካች ሊሆን ስለሚችል የመንሸዋረር ችግር ሲከሰት ምርመራ አድርጎ ከሌሎች ከባድ የጤና ችግሮች ጋር ተያያዥነት እንደሌለዉ ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

#የዓይን_መንሸዋረር_ሲኖር_በአምላክ_ወይም_በርኩስ_መንፈስ_ቁጣ_ይመጣልን?

የዓይን መንሸዋረር ታክሞ መዳን የሚችል የዓይን ጤና ችግር ሲሆን በአምላክ ወይም በርኩስ መንፈስ ቁጣ ወይም ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ የሚመጣ ነገር አይደለም። ስለሆነም ይህን ተገንዝቦ ችግሩ ያለባቸዉንና ግንዛቤዉ የሌላቸዉን ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት እንዲሄዱ ማስረዳት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ ልጆች በእኩዮቻቸዉ ዓይነ ሸዉራራ (ጠንጋራ) እየተባሉ ሲጠሩ የበታችነት ስሜት ሊሰማቸዉና በሂደትም የስነልቦናና በራስ የመተማመን ችግር ሊገጥማቸዉ ስለሚችል በወቅቱ ከማሳከም ባለፈ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቃሉን ከመጠቀም መቆጠብ ያስፈልጋል። ይህን ችግር ከማቃለል አኳያ የመምህራን ሚና ከፍተኛ ነዉ።

(ምንጭ መጽሐፍ:-“የዓይን ጤናና እንክብካቤ” በፕ/ር የሺጌታ ገላዉ ብርሃኑ (በደራሲው ፈቃድ መረጃው ተደራሽ ይሆን ዘንድ ከመጽሐፉ ገጽ 113-122 በከፊል ተወስዶ የተለጠፈ)

 

date: 
Sunday, May 21, 2023 - 03:45

Contact CMHS

College Of Medicine and Health Sciences

Bahir Dar University

 Bahir Dar, Ethiopia

Phone:- +251-0582-9 99275

P.o.box:- 79

e-mail:- collegehealthscience@gmail.com

Institutes

Website Design and Developed by LTTU,ICT Copyright © 2017- Bahir Dar University